Fana: At a Speed of Life!

የኮሙኒኬሽን ስራዎችን በአግባቡ ለመከወን ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሙኒኬሽን ስራዎችን በአግባቡ ለመከወን ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ፥ የሐረሪ ክልል ባዘጋጀው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስልጠና ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የኮሙኒኬሽን ስራዎችን በአግባቡ ለመከወን በመንግስት በኩል ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩን ጠቁመው ይህንኑ ምቹ አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የሐረሪ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በክልሉ ለሚገኙ አመራሮች እና ባለሙያዎች ያዘጋጀው ሥልጠና በዲጂታል ሚዲያና ኮሙኒኬሽን አጠቃቀም ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ጠንካራ የዲሞክራሲ ባህል ለመገንባት ጅምር ስራዎች መኖራቸው እና መንግስት ለማህበራዊ ሚዲያ የሰጠው ትኩረት ለዘርፉ መጎልበት ምቹ አጋጣሚ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል።
በሀገር ውስጥ እና በውጪ የሚገኙ የጥፋት ኃይሎች ከፍተኛ የሆነ ጣልቃ ገብነት እና ከራስ የሚመነጭ የውስጥ ችግሮችን ፈጥኖ አለመፍታት የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ በኩላቸው÷ የኮሙኒኬሽን ሥራ የሁሉም አመራር ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡
ውጤታማ የሆነ የሚዲያ ኮሙኒኬሽን አመራር መፍጠር ወቅቱ የሚጠይቀው ቁልፍ ተግባር መሆኑን ገልጸው÷ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያ ሕዝብን በማቀራረብ፣ ሀገርን በመልካም ጎን በመገንባትና በማስቀጠል ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
አመራሩ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለውን ተሳትፎ ሊያሳድግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.