Fana: At a Speed of Life!

የሃይማኖት አባቶች በሐረሪ ክልል የኢድ አል-አድሀ በዓል የሚከበርበትን ስፍራ በጋራ አጸዱ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በሐረሪ ክልል የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች እና የተለያዩ እምነት ተከታዮች የኢድ አል-አድሀ በዓል የሚከበርበትን ስፍራ በጋራ አጽድተዋል።

በጽዳት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበዓላት ወቅት አንዱ የሌላውን ማክበሪያ ስፍራ በማፅዳት አብሮነትን ወንድማማችነት የማሳየት ልማድ እየዳበረ ይገኛል ብለዋል።

ይህም ሀረር የሰላም፣ የመቻቻል እና የአብሮነት ከተማ መሆኗን አንዱ ማሳያ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

በክልሉ የፀጥታ ችግር እንዳይከሰት እምነት አባቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን በቀጣይም ፅንፈኝነትና የብሔር አክራሪነትን ከመከላከል አንፃር የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ እምነት ተከታዮች ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የሃይማኖት እና የብሔር ብዝኃነታችን ሊከፋፍለን አይገባም፤ ይልቁንም መቻቻልን አንድነትንና አብሮነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በፅዳት መርሐ ግብሩ ላን የተሳተፉ የእምነት አባቶች በበኩላቸው÷ የእስልምና እምነት ተከታዮች በነገው እለት ለሚከበረው የኢድ አል ዓድሃ በዓል ማክበሪያ ስፍራን ማፅዳታቸውን ጠቁመው÷ ይህም ከልብ የመነጨ ፍቅርና አንድነትን ለመግለጽ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም መሰል ተግባራት በማጠናከር በሃይማኖቶች መካከል መቻቻል አብሮነት እና አንድነት ማጎልበት ያስፈልጋል ሲሉ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በመርሐግብሩ ላይ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ሚስራ አብደላን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የሀይማኖት አባቶች ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.