Fana: At a Speed of Life!

ለ157 ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላን አደጋ ሲታወስ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ልክ የዛሬ አንድ ዓመት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ ድንገት ተከሰከሰ።

የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 የሆነው አውሮፕላኑ 149 መንገደኞችንና ስምንት የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ላይ ነበር የተነሳው።

ከስድስት ደቂቃ በኋላ ግንኙነቱን ያቋረጠው አውሮፕላኑ ቢሾፍቱ አካባቢ ሲደርስ መከስከሱ ነበር የተገለፀው።

በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞች በድምሩ ከ33 ሀገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎች ህይወትም በአደጋው ምክንያት ወዲያውኑ ህይወታቸውን ማጣታቸውም የወቅቱ አሳዛኝ ክስተት ነበር።

በወቅቱም የአደጋውን መንስኤ የማጣራት ስራም ቀጥሎ ተካሄደ፤ የመከስከስ አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን እና የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል መቅረፀ ድምፅ ለምርመራ ወደ ፈረንሳይ ተላከ፤ በምርመራውም ችግሩ የአውሮፕላኑ የሶፍትዌር ችግር እንደነበረም ነበር በወቅቱ የተገለፀው።

የአውሮፕላን አደጋውን መንስኤ ሲመረምር የቆየው የኢትዮጵያ ቡድን ትናንት ጊዜያዊ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።

ይህ የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው የአደጋ ምርመራ ውጤት እንደሚያስረዳውም አውሮፕላኑ ከመብረሩ በፊት ሁሉንም የቅድመ በረራ ምርመራዎች እንደተደረጉለት ይጠቁማል።

ከመብረሩ በፊትም ምንም ዓይነት የቴክኒክ ችግር እንደሌለበት መረጋገጡንም ነው ያካተተው።

አውሮፕላኑ የነበረውም ክብደት እና ሚዛን በሚፈቀደው መጠን ውስጥ እንደሆነ በግኝቱ ታውቋል።

አውሮፕላኑን በተመለከተ ቦይንግ ኩባንያ የሰጠው ስልጥና በቂ እንዳልነበር ያነሳው ሪፖርቱ በአጠቃላይ የአውሮፕላኑ የዲዛይን ችግር የአደጋው መንስኤ መሆኑን አረጋግጧል።

እነሆ ኢትዮጵያ ያንን አሳዛኝ ክስተት ካስተናገደች ዛሬ ድፍን አንድ ዓመት የሞላው ሲሆን፥ የተለያዩ የመታሰቢያ መርሃ ግብሮችም በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም በዛሬው እለት በፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት ምልእክት፥ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ የሙት ዓመታቸው በኢትዮጵያ እየተዘከረላቸው ለሚገኙ ቤተሰቦች ብርታትና ጽናትን ተመኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በመልእክታቸው፦ “የዛሬ ዓመት በET302 የአውሮፕላን አደጋ 157 ውድ ሕይወቶችን አጥተናል፤ ቤተሰቦችና ጓደኞች ያጧቸውን ለመዘከር በኢትዮጵያ በሚሰበሰቡበት በዚህ ጊዜ፣ ለአደጋው ሰለባ ቤተሰቦችና ወዳጆች ብርታትና ጽናቱን እንዲሰጣቸው እመኛለሁ” ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.