Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 25 ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በእጣ አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ14ኛው ዙር የ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ̎ለረጅም አመታት ገንዘባችሁን እየቆጠባችሁ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን  በጉጉት ስትጠባበቁ የነበራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡

የእናንተ  ለዚህ ቀን መብቃት ሌሎች በጉጉት እና በተስፋ ለሚጠብቁትም ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

ፍላጎት እና አቅርቦት ባይጣጣሙም በተለይም መኖሪያ ቤት በከተማዋ ከፍተኛ ችግር መሆኑን በመረዳት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የመፍትሔ አቅጣጫዎች እየተቀመጡ መሆኑንም አመላክተዋል።

በዚህም የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ እና ለመፍታት ትልቅ የትኩረት አቅጣጫ ማዕከል ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በብድር ቦንድ ፋይናንስ ከተገነቡ እና ሲገነቡ ከነበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮችን በመዳሰስ ወደ ተግባር መገባቱንም አስረድተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ እጣ የሚያወጣባቸውን  የቴክኖሎጂ ሲስተም መዘርጋቱን ጠቅሰው÷ ይሄ  ሁሉ ጥረት ዕጣው በይፋ እንዲወጣ እና ከአድልኦ ነጻ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ  በፊት የነበረውን ውስብስብ ችግር በጽናት በመቋቋም እድለኞች ለዛሬ ውጤት እንዲበቁ ለሰሩ፣ ላገዙ እና ለታገሱ ባለ እድለኞችም  ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የተለያየ የሃሰት ፕሮፓጋንዳዎችን አምነው ቁጠባቸውን ያቋረጡ እንዳሉ ሁሉ፤ ታጋሾች ፅኑዓን ለዛሬው ባለእድለኝነት በቅተዋል ነው ያሉት፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት ሲያስገነባቸው ከቆዩት ቤቶች ውስጥ በ20/80 መርሐ ግብር 18 ሺህ 648 ቤቶች፣ በ40/60 3ኛ ዙር 6 ሺህ 843 በአጠቃላይ 25 ሺህ 491 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ እንደወጣባቸው ተገልጿል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ያስሚን ወሃቢረቢ በበኩላቸው÷ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት ከ300 ሺህ በላይ ቤቶችን ሰርቶ ማስረከቡን ገልፀዋል፡፡

የባለሶስት መኝታ ቤት በተመለከተ ባለፈው ዙር ዋጋውን እስከ 1 ሺህ 500 ቁጠባ ድረስ በማውረድ በማስተናገድ የቤቶች ቦርድ ፕሮግራሙን መዝጋቱን አስታውሰው÷ በዚህ ዙር ለማስተናገድ አጠቃላይ ሲስተሙን የሚያዛባ በመሆኑ በቀጣይ በልዩ ሁኔታ የሚታይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት÷በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27 ሺህ 195 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52 ሺህ 599 በአጠቃላይ 79 ሺህ 794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዚህ ዙር ዕጣ መካተታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በ20/80 ፕሮግራም የሚካተቱት የ97 ተመዝጋቢዎች ብቻ መሆናቸውንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.