Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ አራተኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ዘመቻ በወላይታ ሶዶ ተጀመረ።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ በክልሉ ያሉ ተቋማት የማህበረሰቡን ሕይወት በሚቀይር ስራ መበርታት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

በፍራፍሬ ምርት የሚታወቀው የደቡብ ክልል ይህንን እድል በሚገባ በመጠቀም ለውጭ ገበያ በበቂ መልኩ ማምረት አለበትም ብለዋል አቶ ርስቱ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ፥ 30-40-30 ፕሮጀክት የትውልድ ቅርስ የሆነው የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ በማጠናከር ተቋሞቻችንን የፍራፍሬ ማዕከል እናደርጋለን ብለዋል።

ይህ አንድ ሰው በቤተሰብ ደረጃ መቶ የፍራፍሬ ዛፍ ሊኖረው ይገባል የሚል ዓላማ የያዘ ባለብዙ ፋይዳ ፕሮጀክት ከድህነት መሻገሪያ ዋነኛ ድልድይ ማለት እንደሆነ ነው አቶ ኡስማን የሚናገሩት።

እንደ ደቡብ ክልል ዘንድሮ ከ1 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን የሚገልፁት አቶ ኡስማን ፥ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ፍራፍሬዎችና የአካባቢ ምህዳር የሚያስጠብቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ ይፋ የተደረገበት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሰቲ በአንድ ጀምበር 10 ሺህ የፍራፍሬ ችግኝ ለመትከል ያቀደ ሲሆን፥ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ እያንዳንዱ አስር ችግኝ እንዲተክል ታቅዷል።

ከችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ባሻገር በዩኒቨርስቲው የሚገኘውን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስም የተሰየመው አንድነት ፓርክ እንዲሁም 550 ሺህ የፍራፍሬና የደን ችግኞችን አካቶ የያዘው ችግኝ ጣቢያ ተጎብኝቷል፡፡

በመለሰ ታደለ እና አበበች ኬሻሞ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.