Fana: At a Speed of Life!

የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያን በሚጥሱ አካላት ላይ  እርምጃ እንደሚወስድ ሚኒስቴሩ አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያን በሚጥሱ አካላት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስጠነቀቀ፡፡

የሲሚንቶ አቅርቦትና ፍላጎት ባለመመጣጠኑ ምክንያት ዋጋው እየናረ፥ ስርጭቱም ባልተገባ መንገድ እየተከናወነ የግንባታውን ዘርፍ ሲፈትነው እንደቆየ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

የፋብሪካዎች ከአቅም በታች ማምረት እና የግንባታው ዘርፍ ማደጉን ተከትሎ የሲሚንቶ ፍላጎት መጨመር ለአቅርቦትና ፍላጎቱ አለመጣጣም ምክንያቶች መሆናቸውንም ነው የጠቆመው፡፡

ከፍላጎት መጨመር ጋር ተያይዞ ደላላዎች፣ አምራቾችና አከፋፋች በፈጠሩት የግብይት አሻጥር ምክንያት ያለው ጥቂት የሲሚንቶ ምርትም በትክክለኛው የግብይት ሂደት እንዳያልፍ በመደረጉ  የሚፈጠረውን የዋጋ ንረትና የግብይቱን ስርዓት ለማስተካከል መንግሥት ሲፈተን እንደቆየም ሚኒስቴሩ አውስቷል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዳለው÷የሲሚንቶ አቅርቦትን ጨምሮ ግብይቱ በትክክለኛው የነፃ ገበያ እስከሚመራ ድረስ የተመረተው ሲሚንቶ በአግባቡ ለተጠቃሚው እንዲደርስ የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

ከሰኔ 17 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባር ላይ የዋለው የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያ ቁጥር 908/2014 የመንግሥት ግንባታ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሲሚንቶ እንዲያገኙ የሚፈቅድ መሆኑንም ከሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

መመሪያው የሲሚንቶ አምራቾች፣ የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን ተግባርና ኃላፊነቶች ያካተተ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

መመሪያው ከሚፈቅደው ውጪ የሲሚንቶ ግብይት ሲፈጽሙ በተገኙ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃዎች እንደሚወሰድም ነው ሚኒስቴሩ  ያስጠነቀቀው፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.