Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ክልሎች እና ተቋማት ለዒድ አል ዓድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች እና ተቋማት ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1ሺህ 443ኛው የዒድ አል ዓድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
 
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለእስልምና እምነት ተከታዮች ባስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ የእምነት ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ የተቸገሩትን ወገኖችን በመርዳት እና በመተሳሰብ መሆን እንዳለበት አመልክቷል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም የእምነቱ ተከታዮች በሃይማኖትና በብሄር ሽፋን የህዝብንና የአገርን ደህንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንዲያጋልጡ አሳስቧል።
 
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1ሺህ 443ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
 
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ ኃይማኖቶች ዘመናትን በተሻገረ መቻቻል፣ አብሮነትና መከባበር ኖረዋል፤ዛሬም በዚሁ ተምሳሌታዊ እሴት በመከባበር እየኖሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ የሀገራችንን ሠላም የማይፈልጉ ኃይሎች አርፈው እንደማይተኙ በመገንዘብ እና የሀገርን ሠላም ለመጠበቅ በጸሎትና በአብሮነት በጋራ በመቆም ሊሆን ይገባል ብሏል።
 
በተመሳሳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 443ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲል መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡
 
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ባስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በጦርነት ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን በህይወት ያጡ ወገኖችን፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን እንዲሁም በየአካባቢያችን የሚገኙ ሚስኪኖችና የቲሞችን በማስታወስ መሆን እንዳለበት አሳስቧል፡፡
 
ከሁሉ በላይ ደስታ እንዲሁም ደስታን እጥፍ ድርብ የሚያደርገው በወንድምና በእህት ላይ ደስታን መፍጠር በመሆኑ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ካለን ነገር ላይ በማካፈል ዒዱን ብሩህ ማድረግ እንችላለን ብሏል የክልሉ መንግስት በመልዕክቱ።
 
የሲዳማ ብሐራዊ ክልላዊ መንግስት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1443ኛው ኢድ አል-ዓደሃ ዐረፋ በዓል አንኳን በሰላም አደረሳችሁ ሲል መልካም ምኞት አስተላልፏል።
 
የኢድ አል-ዓደሃ አረፋ በዓል አከባበር በሙስሊሙ እምነት ተከታዮች ዘንድ አንዱ የትእዛዝ አካል መሆኑን ገልጾ÷ በዓሉን ድሆችን በመመገብና በመደገፍ ማክበር እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
 
በተመሳሳይ የደቡብ ክልል ለመላው የእስልምና ተከታዮች ለ1ሺ 443ኛውን የዒድ አል- አድሀ (ዐረፋ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
 
ክልሉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደ ከዚህ ቀደሙ የጋራ አንድነቱን በማጠናከር እምነቱ በሚያዘው መሠረት አቅመ ደካሞችን በመርዳት ያለውን በማካፈል በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፍ ጠይቋል፡፡
 
በሌላ በኩል በዓልን በማይመች ሁኔታ ላይ ለሚያሳልፉ ወገኖቻችንን ማዕድ በማጋራት አለኝታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል ብሏል።
 
እንደ ሀገር የገጠሙንን አያሌ ፈተናዎች ተሻግረን የሀገራችንን ክብር ከፍ ለማድረግ እርስ በእርስ መተሳሰብ እና መደጋገፍ እንደሚገባም ነው ያመለከተው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.