Fana: At a Speed of Life!

“ከዚህ በፊት እንደነበረው መመሪያን በግልጽ ሳያሳዩ መመሪያው አይፈቅድም” የሚል አካሄድ ተቀባይነት የለውም – የፍትሕ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከዚህ በፊት እንደነበረው መመሪያን በግልጽ ሳያሳዩ መመሪያው አይፈቅድም” የሚል አካሄድ ተቀባይነት የለውም ሲል ፍትሕ ሚኒስቴር አስጠነቀቀ፡፡
ሚኒስቴሩ በአዋጁ አፈጻጸም ዙሪያ ክትትል ባደረገባቸው ተቋማት ላይ ያሉ ክፍተቶችን በተመለከተ ባካሄደው ውይይት÷ ተቋማት የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅን በአግባቡ ሊተገብሩ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ዳሰሳ የተደረገባቸው ተቋማት ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ናቸው።
የአስተዳደር አዋጁ ተቋማት መመሪያን ሲያወጡ ምን ያህል ሕግን ተከትለው ነው? አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ሲሰጡ መርህን የተከተለ ነው ወይ? የሚሉ ጉዳዮችን ያካተተ ነው።
አዋጁ ተቋማት መመሪያን ሲያወጡ ወይም አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ሲያሳልፉ ሕግ ካልተከተሉ ቅሬታ ያላቸው ዜጎች ውሳኔው በፍርድ ቤት እንዲሻር ማድረግ የሚችሉበትን አሰራርም የያዘ ነው ተብሏል።
በፍትሕ ሚኒስቴር የፌደራል ሕጎች ተፈጻሚነት መከታተያ ዳይሬክተር ትብለጥ ቡሽራ እንደገለጹት÷ የፌደራል ተቋማት አዋጁ ላይ ያሉባቸውን ክፍተቶች በመለየት ማስተካከያ እንዲያደርጉ ግብረ-መልስ እየተሰጠ ነው።
“አንድ ተቋም መመሪያ ከማዘጋጀቱ በፊት ተገልጋዩ እንዲያውቀው በተለያዩ አማራጮች በማስታወቂያ ይፋ ማድረግ አለበት” ያሉት ዳይሬክተሯ÷ ከሕዝቡም የሚካተቱ ሀሳቦች ካሉ የመቀበል ግዴታ ተጥሎበታል ብለዋል።
“አንድ ተቋም ያዘጋጀውን መመሪያ ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ አለበት” ያሉት ዳይሬክተሯ በፍትሕ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ላይ እንዲሁም በራሱ በተቋሙ ድረ-ገጽ ላይ ማውጣት እንዳለበትም አክለዋል።
“ከዚህ በፊት እንደነበረው መመሪያን በግልጽ ሳያሳዩ መመሪያው አይፈቅድም የሚል አካሄድ ተቀባይነት የለውም” ነው ያሉት።
በዜጎች ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚገባቸው ደብዳቤዎች እንዲሁም መመሪያዎችን በድብቅ ማውጣት እንደማይቻልም አብራርተዋል።
አዋጁ በተቋማት በአግባቡ ቢተገበር የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በማቃለል ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው÷ ተቋማት ለተግባራዊነቱ መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በአዋጁ አተገባበር ላይ ችግር ያለባቸው ተቋማት እንዲያስተካክሉ ምክረ-ሀሳብ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው ለማስተካከል ፍቃደኛ ያልሆኑት ላይ ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.