Fana: At a Speed of Life!

ፍትሕ ሚኒስቴር የታክስና የጉሙሩክ ወንጀሎችን ለመከላከልና አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር የታክስና የጉሙሩክ ወንጀሎችን ለመከላከልና አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከጉሙሩክ ኮሚሽን፣ ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በዛሬው ዕለት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተፈራርመዋል፡፡
ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በስምምነቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ውጤታማ የታክስ አስተዳደር ለአንድ ሀገር እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና ገቢ ሰብስቦና በጀት በጅቶ ለልማት ማዋል የሚቻለው ገቢ ሲኖር መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህን ገቢ ለማስገኘትም ግብራቸውን በታማኝነትና በሀቀኝነት የሚከፍሉና ሕግ የሚያከብሩ አካላት እንዳሉ ሁሉ የግብር መክፈል ግዴታቸውን በአግባቡ የማይወጡ አካላትን ለሕግ ማቅረብ አስፈላጊ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ይህ እውን እንዲሆን ስምምነቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው÷ ስራዎችን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ መስራት ከተቻለ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ እንደገለጹት÷ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በኢኮኖሚ ሴክተሩ ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ ለመቀልበስ የፍትሕና የፀጥታ አካላት በጋራ በሠሩት ሥራ ሊደርሱ የሚችሉ ከባድ አደጋዎችን ማስቀረት ተችሏል ማለታቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ወደ ፊትም የበለጠ ተቀናጅቶ በመስራት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ስምምነቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
የስምምነቱ ዋና አላማም የታክስና የጉሙሩክ ሕግ እንዲከበር በማድረግ የታክስ አስተዳደሩን የበለጠ ውጤታማ በማድረግ÷ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት መሰብሰብ እና ኮንትሮባንድንና ሕገ ወጥ ንግድን መቆጣጠር፣ ፈጣንና የተደራጀ የመረጃ ቅብብሎሽ ስርአት እንዲፈጠርና እንዲጠናከር በማድረግ የሕግ ተገዥነትን ማጠናከርና የተቋማቱን የሕግ ማስከበርና የሕግ ማስፈፀም አቅም ማጠናከር መሆኑ ተገልጿል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.