Fana: At a Speed of Life!

የፕላን በጄትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማትን የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ገመገመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ በማዘጋጀትና ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች የ10፣ የ5 እና የአንድ ዓመት ዕቅድ እንዲያዘጋጁ በማድረግ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያከናወነው ተግባር በጠንካራ አፈጻጸም የሚጠቀስ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን እና የተጠሪ ተቋማትን የ 11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡
ክፍተት ያለባቸው መመሪያዎች እንዲሻሻሉ መደረጉና የአዋጭነት ጥናቶች በትኩረት መተግበራቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የዋጋ ግሽበት በኢኮኖሚው ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠር የሚያስችል ፕሮግራም በመንደፍ እንዲሁም ገፊ ምክንያቶችን በመለየትና በመተንተን የሚደረጉ ጥናቶች ፋይዳቸው የላቀ መሆኑ በ11 ወራቱ አፈጻጸም የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአበረታች አፈጻጸም ተጠቅሰዋል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነትና መደጋገፍም በበጎ ጎኑ ተነስቷል፡፡
ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ ረገድ ያለውን አፈጻጸም ቋሚ ኮሚቴው በእጥረት ያስቀመጠ ሲሆን÷ ከአስፈጻሚ አካላት የሚመጡ ሪፖርቶችን በተቀመጡ መለኪያዎች መሰረት አለመለካትም ሌላው ጉድለት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ እና ሚኒስቴሩ ስለሚሰራቸው ሌሎች ተግባራት በቂ ትኩረት ሰጥቶ ስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እንዲሰራም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.