Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በአፍጋኒስታን የሚገኙ ወታደሮቿን ማስወጣት ጀመረች

አዲስ አበባ፣መጋቢት 1፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በአፍጋኒስታን የሚገኙ ሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን ማስወጣት ጀምራለች።

አሜሪካ እና በአፍጋኒስታን የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ታሊባን በቅርቡ በሀገሪቱ ሰላም ማስፈን የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

በድርድሩ አሜሪካ በሀገሪቱ ያሰማራቻቸውን 12 ሺህ ወታደሮች ወደ 8 ሺህ 600 ዝቅ ለማድረግ ተስማምታለች።

በዚህ መሰረትም አሜሪካ ተቀናሽ የሚሆኑ ወታደሮችን ከስፍራው ማስወጣት መጀመሯ ነው የተገለጸው።

ከ10 ቀናት በፊት ሁለቱ ወገኖች ባካሄዱት የድርድር መድረክ ላይ የአፍጋኒስታን መንግስት አለመሳተፉ  ተገልጿል።

በቀጣይ ታሊባን እና የአፍጋኒስታን መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማስፈን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

በአንጸሩ ታሊባን ከአፍጋን መንግስት ጋር ውይይት ለማድረግ በእስር ላይ የሚገኙ አባሎች እንዲፈቱ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ ነው የተገለጸው።

የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ በበኩላቸው ታጣቂ ቡድኑ ውይይት ለማድረግ ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የአፍጋኒስታን መንግስት 1 ሺህ የሚደርሱ የታሊባን ታጣቂ ቡድን አባላት እስረኞችን በተያዘው ሳምንት ለመፍታት መወሰኑ ተመላክቷል።

አሜሪካ በአፍጋኒስታን ሰላም ለማስከበር ካሰማራቻቸው ወታደሮች ውስጥ እስካሁን 2 ሺህ 400 በላይ የሚሆኑት መገደላቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ምንጭ፥አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.