Fana: At a Speed of Life!

የመመሪያ ጥሰት በፈጸሙ 96 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካምፓሶች ላይ የእርምት እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመመሪያ ጥሰት በፈጸሙ 96 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካምፓሶች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ በተለያዩ የክልል ከተሞች በሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትላይ ባካሄደው ድንገተኛ ፍተሻ ከመመሪያ ውጪ ተማሪ ተቀብለው ሲያስተምሩ ባገኛቸው ካምፓሶች ነው የእርምት እርምጃ የወሰደው፡፡
ጥሰቶቹም የእውቅና ፈቃድ ባልተሰጠባቸው ካምፓሶች እና የትምህርት መስኮች ተማሪ ተቀብሎ ማስተማር፣ እንዲያስተምሩ ባልተፈቀደበት የትምህርት አሰጣጥ ክፍለ ጊዜ ተማሪ መዝግበው ለማስመረቅ ማስተማር፣ ፈቃድ ባገኙበት ካምፓስ (ህንጻ) ላይ አለመገኘትን ያካትታል፡፡
በተጨማሪም በእውቅና ፈቃድ እና በእውቅና ፈቃድ እድሳት ወቅት ተሟልተው የነበሩ ግብዓቶችን አጓድለው መገኘታቸውን እና ያልተፈቀደላቸውን የደረጃ ስያሜ መጠቀም እና የመሳሰሉት ጥሰቶች በድንገተኛ ፍተሻ የተረጋገጡ መሆናቸውን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
በተወሰደው ርምጃ መሰረትም ለተቋማቱ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ በፕሮግራም፣ በካምፓስና በተቋም ደረጃ የእውቅና ፈቃዳቸው ተሰርዞ ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጉ፣ ከህግ-ውጪ የተቀበሉትን ተማሪዎች እንዲያሰናብቱ ተደርጓል፡፡
በተጨማሪ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን የእውቅና ፈቃድ ወዳላቸው ተቋማት እንዲያያዛውሩ፣ እንዲሁም የመመሪያ ጥሰት በፈጸሙበት አካባቢ እና የትምህርት መስኮች ከ2 እስከ 3 ዓመት የእውቅና ፈቃድ እንዳይጠይቁ ማድረጉንም ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
ተማሪዎች፣ ወላጆች እና መላው ህብረተሰብ በህገ-ወጥ መንገድ የሚፈጸመውን የተማሪ ምዝገባ የሚያደርሰውን የጊዜ፣ የገንዘብና ሞራላዊ ኪሳራ በመገንዘብ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ እንዲሁም ለባለሥልጣኑ ጥቆማ በማቅረብ የበኩላቸውን እንዲወጡም ባለስልጣኑ አሳስቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.