Fana: At a Speed of Life!

በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃቶች በዘላቂነት ለመከላከል መንግስት በተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ቡድኖችና ጽንፈኞች በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት በዘላቂነት ለመከላከል መንግስት በተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ፡፡
አቶ ተስፋዬ÷ በምዕራብ ወለጋ በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸም የማይገባው አስነዋሪ ጭፍጨፋ በንጹሃን ዜጎች ላይ መፈጸሙ ልብ ሰባሪ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በጽንፈኞችና በሽብር ቡድኖች የሚፈጸሙ ንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለመግታትና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የችግሩን ምንጭ መረዳት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ዋነኛ የችግሩ ምንጭም አብሮነት እንዲሸረሸርና ኢትዮጵያ እንድትኮስስ ታስቦ ለዘመናት ሲሸረብ የቆየ የፖለቲካ ሴራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የሚንዱ ስራዎች ለዓመታት መሰራታቸውንና በምትካቸው ፅንፈኝነት ሲዘራ መቆየቱን ገልጸው÷ ይህም ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ወቅቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የሚከናወንበት በመሆኑ÷ ይህን በማደናቀፍ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትለማ ርብርብ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት በቆሙባቸው ጊዜያት ሁሉ ፈተናዎቻቸውን በድል መወጣታቸውን አስታውሰው÷ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ማንበርከክ የሚቻለው የሕዝቦቿን አንድነት በመሸርሸር ነው የሚል አቋም ይዘው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ነው አቶ ተስፋዬ ተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ጠላቶች ሕዝብና መንግስትን ለመነጠል ያለ እንቅልፍ እንደሚሰሩ ጠቁመው÷ የመሪዎችን ንግግር ከአውድ ውጭ እየተረጎሙ ጭምር ችግር ለመፍጠር እንደሚሞክሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የፀጥታ መዋቅሩን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለመከፋፈልና ኢትዮጵያን ለማዳከም በርካታ ስራዎች ቢሰሩም÷ የፀጥታ ኃይሉ ከኢትዮጵያዊነቱ ዝንፍ የማይል መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚመጥን የጸጥታ አካል ለመገንባት ታስቦ የተተገበረው ሪፎርም ስኬታማ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል::
መንግስት ለዴሞክራሲና ለሰላም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያን ለማፅናት የተቋማት ግንባታ ላይ አትኩሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ድል በጋራ መቆም ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ተገንዝበው እጅ ለእጅ በመያያዝ የዳገቱን ጉዞ በስኬት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.