Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ያስቀመጠውን የሰላም አማራጭ ተግባራዊ በማድረግ በአገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ ይገባል -የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ያስቀመጠውን የሰላም አማራጭ ሁሉም ወገኖች ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ገለጹ።

መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት በመወሰን ይህንኑ ስራ በዋናነት የሚያከናውን ሰባት አባላት ያሉት ቡድንም ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡

የሰላም ሂደቱም ሕገ መንግሥታዊ መርሆን ያከበረ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር የማያቀርብና ሂደቱም በአፍሪካ ኀብረት አስተባባሪነት የሚመራ እንዲሆን አቋም መያዙን የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት ውሳኔ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ የቀጣናው ዋነኛ የሰላምና ደህንነት ጠበቃ መሆኗን አስታውሰዋል።

ዶክተር ሙላቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራትና ጎረቤቶቿም ከግጭት ይልቅ ሰላም እንደሚበጃቸው አቋሟን በጽናት በማራመድ እንደምትታወቅ ጠቅሰው፥ ከዚህ አኳያ አሁን ያጋጠማትን ችግር በመፍታት ወደ ሰላም እንድትመለስ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው ይላሉ።

ለዚህም መንግሥት የሰላም አማራጭ ውሳኔ ማሳለፉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፥ ለኢትዮጵያ ሰላም ከኢትዮጵያውያን ውጭ ማንም ነጋሪ እንደማያስፈልግ ነው ያነሱት።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፥ መንግሥት የተከተለው የሰላም ውሳኔ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ጦርነት ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላት የገለጹት አቶ ኃይለማርያም፥ በጦርነት የሚሳተፍ የትኛውም አካል ከጦርነት ማትረፍ እንደማይችል ነው ያብራሩት፡፡

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ጦርነትና ግጭት ሊቆም እንደሚገባና ችግሮችን በሰላም መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አውስተዋል።

ሰላምን በማስፈንም ህብረተሰቡን ከስጋትና ከጭንቀት እንዲሁም ሀገሪቱን ከተጨማሪ ጉዳት ማላቀቅ እንደሚገባም እንዲሁ።

የቀድሞዎቹ መሪዎች አክለውም፥ የቀጣናው ሀገራት፣ አፍሪካና የዓለም ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ለሰላምና ደህንነት ትልቅ ሚና እንደምታበረክት ያውቃሉ፤ ለዚህም ከእኛ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ያሉባትን ውሰጣዊ ችግሮች በውይይት በመፍታት ሰላሟን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው ስራ እንዳልሆነም አብራርተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለቀጣናው፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላምና ደህንነት ያላትን ጉልህ ሚና ማስቀጠል እንደሚገባት ነው የተናገሩት።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የሀገራችን አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም ጠብመንጃን ወደ ጎን ትቶ በውይይት መፍታት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት ።

በዚህም በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ለመትከል ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.