Fana: At a Speed of Life!

ማህበራዊ ትስስርን ለማስፈን ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለወጣቱ ማስተላለፍ እደሚገባ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ አንድነትና ማህበራዊ ትስስርን ለማስፈን ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለወጣቱ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ፡፡

አራተኛው ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የተማሪዎች መርሐ ግብር በጅማ፣ ሀዋሳ እና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች ተጀምሯል፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጻነት ወርቅነህ እንዲሁም ተማሪዎች እና እንግዶች በተገኙበት ተጀምሯል፡፡

አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ለህሊና እርካታ ለማግኘት የሚገባበት ተግባር መሆኑን ገልፀው÷ እናንተም በገጠርና ከተማ ወጥታችሁና ወርዳችሁ ማህበረሰባችሁን ለማገልገል በመምጣታችሁ ኮርተንባችኋል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች÷ ሰብዓዊነትን በመላበስ በፍቅርና በርህራሄ ፣ መስዋዕትነት ለመክፈል በመዘጋጀት ሰላምን ለመስበክ መዘጋጀት ይገባችኋል ብለዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ በበኩላቸው÷ ወጣቶች ዕለት ተዕለት ለሀገራቸው ማሰብ እና ያሰቡትን መተግበር እንደሚገባቸው አንስተዋል።

ሀገርን ለማገልገል ዕድል ያገኛችሁ ወጣቶች ሥራችሁ በታሪክ የሚመዘገብ በመሆኑ÷ ልትደሰቱ ይገባል ዩኒቨርሲቲውም በቤተሰባዊነት ስሜት ከጎናችሁ ነው ብለዋል።

እስካሁን በበጎነት ለአብሮነት የወጣቶች ብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ23 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመላው ሀገሪቱ ተሰማርተው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በስልጠናው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 3 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስልጠና እንደሚሰጥ ተገልጿል።

በተመሳሳይ በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን የሐዋሳ ዩኒቨርቲውን የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ስልጠና ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር እንዳሉት÷ መርሐ ግብሩ የወጣቱን አመለካከት፣ ክህሎትና ሞራል በመገንባት እንዲሁም አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲገነዘብ በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር ብሎም ለሀገራችን ሰላምና አንድነት መጠናከር የጎላ ሚና አለው፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶገነት ካምፓስ 1 ሺህ 500 በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች የስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን÷ ስልጠናው ከአንድ ወር በላይ እንደሚቆይ ተመላክቷል።

በተመሳሳይ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው መርሐ ግብር ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ÷ መርሐ ግብሩ የስነልቦና የክህሎት ስልጠናዎችን እንዲሁም አዳዲስ ሐሳቦችን እንደሚካትት ጠቁመው ተማሪዎች ስልጠናውን በሚገባ እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡

ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተማሪዎች በጋራ የበጎ ፈቃድ ስራ የሚሰሩበት የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተጀመረ አራት ዓመታትን ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ 2 ሺህ 500 ተማሪዎችን ለሚቀጥሉት 45 ቀናት ለማሰልጠን በዛሬው ዕለት “በጎነት ለአብሮነት” በሚል መሪ ሐሳብ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

“በአዕምሮ ብስለት፣ ስራ ፈጠራ፣ ዕድሎችን መጠቀም፣ ሀገራዊ አንድነትና ሰላም እና መሰል ርዕሶች ላይ ያተኮረ ስልጠና እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

በጥላሁን ይልማ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.