Fana: At a Speed of Life!

በጎንደር ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎንደር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ወርቅነህ አያል ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ÷ ፕሮጀክቱ የከተማውን የውሃ አቅርቦት ሽፋን ከ18 በመቶ ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በከተማው አሁን ላይ 70 ሺህ ሜትር ኪዩብ የንጹህ መጠጥ ውሃ በቀን የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመው÷ እየቀረበ ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ ከ13 ሺህ ሜትር ኪዩብ እንደማይበልጥ ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት ነዋሪዎች በ15 ቀን አንድ ቀን ብቻ ውሃ በፈረቃ እንዲያገኙ መገደዳቸውን ጠቁመዋል።

የመገጭ የመስኖና የንጹህ መጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት በተያለዘት ጊዜ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ እየተባባሰ የመጣውን የከተማውን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የአስቸኳይ ጊዜ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት መተግበር ማስፈለጉንም ገልጸዋል።

የውሃ አቅርቦት ችግሩ ጊዜ የሚሰጥ ባለመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ የአስቸኳይ ጊዜ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮጀክት በማስጠናት ፕሮጀክቱን የሚያስፈጽሙ አንድ አብይና ሁለት ንዑሳን ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው÷ ፐሮጀክቱ በአካባቢው ያሉ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

የከተማው ነዋሪዎች፣ በውጪ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የፕሮጀክቱን ወጪ በመሸፈን በኩል ድጋፍ እንዲያደርጉ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴው እንደሚሰራም አመላክተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በቀን ለነዋሪዎች እየተሰራጨ ያለውን 13 ሺህ ሜትር ኪዩብ የመጠጥ ውሃ ወደ 45 ሺህ ሜትር ኪዩብ ለማሳደግ ያስችላል ተብሏል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.