Fana: At a Speed of Life!

“ስሪ ፖይንት” ከመስከረም ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ የታዳጊዎች እግር ኳስ ስልጠና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጀርመኑ ስሪ ፖይንት ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵያ የታዳጊዎች እግር ኳስ ስልጠና መስጠት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታወቀ።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንደገለጹት÷ የስልጠና ማዕከላት ከፍቶ ታዳጊ ወጣቶችን ማሰልጠን የክለቦችና የግለሰቦች ኃላፊነት ቢሆንም አሁን ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ በተቃራኒው ነው።
ለዚህ ደግሞ የሀገሪቱ የእግር ኳስ ክለቦች አደረጃጀትና የስራ ፍቃድ አሰጣጥ ያልተስተካከለ መሆኑ ክለቦች በሚጠበቅባቸው ልክ እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል።
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት በሚችለው አቅም ታዳጊዎችን በስፋት ለማብቃት የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም ፌዴሬሽኑ በጥር ወር 2014 ዓ.ም ስሪ ፖይንት ከተባለና በሕጻናት እግር ኳስ ስልጠና ላይ ከሚሰራ የጀርመን ድርጅት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የታዳጊዎች እግር ኳስ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት መፈጸሙን ተናግረዋል።
በዚህም ድርጅቱ ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም አንስቶ ስልጠና መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል።
ስሪ ፖይንት በስልጠናው ታዳጊዎችን በማብቃት ለአውሮፓና በሌሎች ሀገራት ለሚገኙ ክለቦች በማዘዋወር ከሚገኘው ገንዘብ 60 በመቶውን የሚወስድ ሲሆን÷ ቀሪውን 40 በመቶ ፌዴሬሽኑ የሚያገኝ ይሆናል።
የፌዴሬሽኑ ግብ በዋናነት ከሚገኘው ገንዘብ ይልቅ ታዳጊዎቹ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች እድል አግኝተው ራሳቸውና ቤተሰባቸውን አለፍ ሲልም ሀገራቸውን የሚጠቀሙበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
ለስልጠና የሚገቡ ታዳጊዎች ምልመላ በቅርቡ በሚካሄደው የክልሎችና ክለቦች ከ17 ዓመት በታች ውድድር እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
ለስልጠናው ብቁ ሆነው የሚመለመሉት ታዳጊዎች በየጊዜው እየተመዘኑ በሚያስመዘግቡት ውጤት መሰረት የመተካት ሂደት እንደሚኖር ነው የተናገሩት።
ስልጠናው በጊዜያዊነት በአዲስ አበባ አያት አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልህቀት አካዳሚ እንደሚሰጥ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.