Fana: At a Speed of Life!

የኢድ አል አድሀ በዓልን በማስመልከት ለ1 ሺህ 800 ወገኖች የማዕድ ማጋራት ስነ ስርዓት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የ1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል አድሀ በዓልን በማስመልከት ለ1 ሺህ 800 ወገኖች የማዕድ ማጋራትና ምሳ ማብላት ስነ ስርዓት ተከናወነ፡፡
የወንድም ካሊድ ፋዉንዴሽን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የዳያስፖራ ኤጀንሲ፣ በድረ ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ማህበር እና ሌሎች በጎ ፈቃደኛ አካላት በጋራ በመሆን ከተለያዩ መርጃ ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኛ አካላት በተገኘ ድጋፍ ነው የማዕድ ማጋራቱ የተከናወነው፡፡
የማዕድ ማጋራቱም÷ ለ1 ሺህ 800 አቅመ ደካሞች፣ ለችግር ተጋላጭ ወገኖች፣ ሴቶች፣ አረጋውያን፣ ሕጻናት እና አካል ጉዳተኞች በካሊድ ፋውንዴሽን ምግባረ ሰናይ ድርጅት መካሄዱን ከሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ስነ-ስርዓቱ በካሊድ ፋውንዴሽን ምግባረ ሰናይ ድርጅት የተከናወነ ሲሆን÷ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ወንድም ካሊድ እና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት÷ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፉ ቢሆንም እናቶቻችንና አባቶቻችን ያወረሱንን መተባበር፣ መደማመጥ፣ መከባበር እና መተዛዘን አጠናክረን ከቀጠልን የማንሻገረው ፈተና እንዳማይኖር የዛሬው የአብሮነት ስነ-ስርዓት ህያው ምስክር ነው ብለዋል፡፡

የዘንድሮ የኢድ አል አድሀ (አረፋ) በዓልን በማስመልከት የማዕድ ማጋራት ስነ ስርዓት እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና ያቀረቡት ወንድም ካሊድ በበኩላቸው÷ ስነ-ስርዓቱ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ገልጸዋል፡፡

ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪ ዋና ዓላማው ዳያስፖራው ሀገሩን እንዲያውቅና እንዲያስተዋውቅ እንዲሁም ወገኑን በሀሳብና በሌሎች  እንዲደግፍ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ ናቸው፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.