Fana: At a Speed of Life!

የዴሞክራሲ ተቋማት የማሻሻያ የለውጥ ስራዎችን የተመለከተ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል ኦዲተርና የመገናኛ ብዙኃን የማሻሻያ የለውጥ ስራዎችን የተመለከተ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎ ፥ የዴሞክራሲ ተቋማት ምክር ቤቱ በሕገ መንግስቱ የተሰጠውን ስልጣን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ክንፎች ናቸው ብለዋል።

ተቋማቱ የሰብዓዊ መብት መጠበቅን ለማረጋገጥ፣ አስተዳደራዊ በደሎችን ለመቅረፍ፣ የሃብት አስተዳደርን በአግባቡ ለመጠቀምና የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት እንዲሁም የህዝብ ድምጽን ለማሰማት እነዚህ ተቋማት ወሳኝ ናቸው ነው ያሉት።

ተቋማቱ በአገሪቱ ለተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ከፍተኛ አቅም ሆነዋል ያሉት አፈ ጉባኤው ፥ ሠላምን በዘላቂነት ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ የዴሞክራሲ ተቋማት ራሳቸውን በሠው ኃይልና በተቋም የለውጥ አደረጃጀት በሰፊው መገንባት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።

በጥቂት ጸረ ሰላም ኃይሎች የሚፈጸሙ ችግሮችን በአንድነት በመቆምና ህመሙን በጋራ በማከም መፍትሔ ማምጣት ይጠበቅብናልም ብለዋል።

በየትኛውም ጊዜ አብሮ መቆም የታሪክ አካላችን ነው ያሉት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ፥ በአንድነት በመቆም ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመድረኩ ላይ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌደራል ኦዲተር፣ የመገናኛ ብዙኃንና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.