Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ 27 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበለትን የተጨማሪ በጀት ረቂቅ ለዝርዝር እይታ መራ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባውም በተለያዩ ረቂቆች ላይ በመወያየት ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው መደበኛ ስብሰባውም 27 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበለትን የ2012 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅን ተመልክቷል።

በዚህም ተጨማሪ በጀቱ መሰረታዊ መነሻ የሆነው በመንግስት የተዘጋጀ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሆኑ ተጠቁሟል።

የረቂቅ በጀቱ ዋና አላማ ኢኮኖሚው አሁን ከገጠሙት ተግዳሮቶች የሚላቀቅበት የፖሊሲ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ 18 ቢሊየን ብር፣ ለልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ትግበራ 2 ቢሊየን ብር፣ ለእኩል ስራ እኩል ደመወዝ ሀገራዊ ትግበራ 7 ነጥብ 9 ቢሊየን በድምሩ 27 ነጥብ 8 ቢሊየን ተጨማሪ በጀት ሆኖ ነው የቀረበው።

የ2012 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት እና የወጭ አሽፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ የተጀመረውን ሃገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚያግዝ መሆኑ በምክር ቤቱ ቀርቧል።

ምክር ቤቱም ረቂቁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ እና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ለሁለተኛው ሃገር አቀፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሃይጂን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ፣ በኢትዮጵያና እና በኮሪያ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ መካከል ለአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል መመስረቻ ማስፈጸሚያ እንዲሁም በኢትዮጵያና እና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ለደብረ ማርቆስ ሞጣ የመንገድ ስራ ማሻሻያና ማሳደጊያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረጉ የብድር ስምምነቶች ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የወጣ የነጠላ ኦዲት ረቂቅ አዋጅ እና የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብን መርምሮ ለመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት እንዲሁም በተባባሪነት ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በተመሳሳይ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን ረቂቅ አዋጅ ላይም በመምከር ለዝርዝር እይታ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.