Fana: At a Speed of Life!

የሕዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ የክልሉ መንግስት በሙሉ አቅሙ እየሠራ መሆኑን አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝቡን የመሰረተ ልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የክልሉ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ በሙሉ አቅሙ እየሠራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

በአዳማ ከተማ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተሠሩ 119 የልማት ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል 257 የቁጠባ ቤቶችን ጨምሮ የአዳማ ቀለበት መንገድ የአስፋልት ኮንክሪት፣ የቡኡራ ቦሩ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የውስጥ ለውስጥ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና አስፋልት፣ የጎርፍና ፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮችና የእግረኛ መንገድ ይገኝበታል።

አቶ ሽመልስ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በክልሉ ማነቆ የሆኑብንን የአሸባሪው ሸኔ ፈተናን ተቋቁመን የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የሰላምና የጸጥታ ችግሮችን ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በትብብር እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት በገጠርና ከተማ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ማስፋፋት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና መለወጥ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩን አሁንም ልዩ ትኩረት በመስጠት በስፋት ወደ ኢንቨስትመንት ማስገባት አለብን ያሉት አቶ ሽመልስ÷ ለዚህም አሁን ካለበት በተሸለ መልኩ በከተሞች የኢንቨስትመንት ቦታዎች ሊመቻችላቸው ይገባል ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ እንደገለጹት÷ አሸባሪው ቡድን በክልሉ ላይ የደቀነውን ፈተና ተቋቁመን የመረቅናቸው መሰረተ ልማቶች የሕዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያረጋግጡ ናቸው።

የክልሉን ሕዝብና ባለሃብቶች አቅም በማቀናጀት በዜግነት አገልግሎት እንዲሳተፉ በማድረግ ለብልጽግና መሰረት መጣል የሚችሉ ስራዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው÷ በዘንድሮው ዓመት ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ በሆነ ወጪ ከ133 በላይ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጀምሮ 119 የሚሆኑት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደበቁ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተለይ የከተማዋን አገልግሎት ወደ ዲጂታል ለመቀየር “አዳማ ስማርት ሲቲ” እውን ለማድረግ 175 ሔክታር የከተማዋን ገፅታ ሙሉ በሙሉ ለመለወጥ የዲዛይን ስራ በሀገር ውስጥና በውጭ ምሁራን ጭምር በማስጠናትና በማዘጋጀት ለባለሃብቶች ምቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በነበረው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ እንደነበር ጠቁመው÷ በዚህም ከሕዝቡ በጥሬ ገንዘብ 280 ሚሊየን ብር ለልማቱ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.