Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል በ2014 በጀት ዓመት ከገቢ ግብር 7 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጸሑፍ እንደገለጹት÷በክልሉ የነበሩ ችግሮችን በመቋቋም ለመሰብሰብ ከታቀደው ገቢ  95 ነጥብ 5 በመቶ  የሚሆነውን ማሳካት ተችሏል፡፡

አቶ ሙስጠፌ ÷ ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት ብቻ 18 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገቢ እንደ ተሰበሰበ አስታውሰው÷ ይህም ከለውጡ በፊት ከነበሩት 10 ዓመታት የ10 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

ሁኔታው የክልሉ መንግስት የመፈጸም አቅም መጠናከሩን እንደሚያሳይ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ  አጽንኦት የሰጡት።

እየተካሄደ ባለው የክልሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የክልሉ የገቢዎች ቢሮ የአፈፃፀም ሪፖርት መቅረቡንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.