Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በ2015 በጀት ዓመት ነባር ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በ2015 በጀት ዓመት ነባር ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግስት በጀት አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማዋ የ2015 ረቂቅ በጀት ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ነጂባ አክመል÷በበጀት ዓመቱ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ለትምህርት፣ ለውሃ፣ ለመንገድ፣ለትራንስፖርት፣ለጤና እና ለሌሎችም ፕሮጀክቶች በልዩ ትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

የከተማዋ የ2015 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 100 ቢሊየን 56 ሚሊየን ብር እንዲሆን በካቢኔው በቀረበው ረቂቅ ላይ በከተማዋ ምክር ቤት ውይይት ተደርጓል።

በረቂቅ በጀቱ፣ለካፒታል በጀት 53 ቢሊየን ብር፣ ለመደበኛ ወጪ 42 ነጥብ 75 ቢሊየን ብር፣ለመጠባበቂያ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ሆኖ ቀርቧል።

ከረቂቅ በጀቱ 70 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር በከተማው በማዕከል ደረጃ ለአስፈጻሚ አካላት እና 29 ነጥብ 79 ቢሊየን ብር ለክፍለ ከተሞች በድጎማ የሚሰጥ መሆኑን የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል።

ከተያዘው በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት የሚውል የካፒታል በጀት መሆኑንም ገልጸዋል።

ረቂቅ በጀቱ በከተማ አስተዳደሩ የተቀመጡ የልማት ግቦችን ለማሳካት የመንግስት ኃብት ቅድሚያ ትኩረት ለተሰጣቸው ዘርፎች መሰረተ ልማት፣ለፈጠራ እና ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት የከተማን ነዋሪ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች የበለጠ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ጠቁመው÷የመሰረተ ልማት፣የመኖሪያ ቤት፣የጤና፣እና ዘላቂ ልማት ተግባራትን በተመለከተ ትኩረት ሊያገኙ ይገባልም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጋትዎች ዋር÷ ከተማ አስተዳደሩ ወጪውን በራሱ የሚሸፍን በመሆኑ በገቢ አሰባሰብ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት አብራርተዋል።

በረቂቅ በጀቱ አብዛኛው ለካፒታል በጀት የሚውልና የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚውል መሆኑን የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊዋ ገልጸዋል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ ባለፈ አዳዲስ ፕሮጀክቶች የሚጀመሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.