Fana: At a Speed of Life!

የአጋሮ ከተማ የመጠጥ ውሃ ችግርን ለመፍታት የ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የውሃ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)በጅማ ዞን የአጋሮ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት በ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ተፈረመ፡፡

የጅማ ዞን ውሃና ኢነርጂ ጽህፈትቤት ሃላፊ አቶ መሃመድ ከድር እንደገለፁት÷ ለበርካታ ዓመታት የህብረተሰቡ የቅሬታ ምንጭ የነበረውን የውሃ ፕሮጀክት ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከዓለማየሁ ተፈራ የግል ስራ ተቋራጭ ጋር ስምምት ተፈርሟል፡፡

ተቋራጩ በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ የውሃ ፕሮጀክቱን አጠናቆ ለማስረከብ ውል መፈራረማቸውንም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

የህብረተሰቡን ችግር ይፈታል የተባለው ይህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክት ከአዌቱ ወንዝ የሚሳብ ሲሆን÷በአጠቃላይ የከተማ ውስጥን ጨምሮ 65 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ገልጸዋል ።

በተጨማሪም ከትላልቅ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን ህብረተሰቡን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ 912 ጥቃቅን የህንድ ፓምፖችን የመስራት እና የመጠገን ስራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡

የአጋሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ናስር መሀመድአሚን በበኩላቸው÷ የህብረተሰቡን ችግር በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ የታለመው ፕሮጀክቱ በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል ።

ተስፋሁን ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.