Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በስንዴ ምርት አሸናፊ ትሆናለች – ቢልለኔ ስዩም

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በስንዴ ምርት አሸናፊ እንደምትሆን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በኬንያው ኔሽን ጋዜጣ ላይ በጻፉት ጽሁፍ ገለጹ።

ኃላፊዋ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለምን አሸናፊ ለመሆን እንደምትበቃ ባብራሩበት ጽሑፍ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት ከመቋቋም ጎን ለጎን፥ ሀገሪቱ በተለያዩ የልማት መስኮች ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ እድገት ካስመዘገበችባቸው ዘርፎች መካከል ደግሞ በግብርናው ዘርፍ ውስጥ የሚገኘው የስንዴ ምርት አንዱና ዋነኛው ክንውን መሆኑን ጠቅሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግስት ኢትዮጵያን ለመለዋጥ በምግብ እህል ራሷን መቻል እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት ቁልፍ ጉዳይ አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ነው በአጽንኦት ያስረዱት።

ጥራት ያለው እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ተግበራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ በአስር አመት የልማት መሪ እቅድ እንደ ግብርና ባሉ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጋ በመንቀሳቀስዋ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗንም አብራርተዋል፡፡

በተለይ በዚህ ዘርፍ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደ ስንዴ ያሉ ዋና ዋና የግብርና ምርቶችን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የማስቀረት ጽኑ ፍላጎት መኖሩንም አመላክተዋል፡፡

በማደግ ላይ ላለች እና በየጊዜው እያደገ የሚመጣ የወጣት ቁጥር ላለባት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን መቻሏ እና ከውጨ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ትልቅ ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአየር ንብረት ለውጥና ለተደጋጋሚ ድርቅ ተጋላጭ የሆነው የኢትዮጵያ ግብርና ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሻሻሉ ፖሊሲዎች ምክንያት በፍጥነት መቀየሩንም አንስተዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበሩ የግብርና ፖሊሲዎች በበልግ እና በመኸር የሰብል ወቅቶች ጥገኛ እንደነበሩ ገልጸው፥ ባለፉት ሶስት ዓመታት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግስት የበጋ ስንዴ ምርትን በብዛት ለማምረት ሰፊ እንቅስቃሴ ማድርጉን ነው ኃላፊዋ ያብራሩት።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.