Fana: At a Speed of Life!

የተቋማቱ ትብብር የቱሪዝም ዘርፉ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለውን ሚና በብቃት እንዲወጣ ያስችላል- ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሁለቱ ተቋማት ትብብር በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማቅረብና የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የቱሪዝም ዘርፉ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለውን ሚና በብቃት እንዲወጣ ያስችላል ሲሉ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የቱሪዝም ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ በጋራ ለመስራት የተስማሙባቸው የትብብር መስኮችም÷ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ ልማት፣ የስራ ዕድል ፈጠራና የስራ ፈጣሪነት አስተሳሰብ እንዲሁም የሙያ ደህንነትና ጤንነት መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ወ/ሮ ሙፈሪሃት በስምምነቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ከዚህ ቀደም ሁለቱ ተቋማት በስልጠናና ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ጅምር ጥረቶች እንደነበራቸው አስታውሰው÷ የአሁኑ ስምምነት ስራውን በላቀ ደረጃ ተቋማዊ መልክ እንዲይዝና እና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ ነው ማለታቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የሁለቱ ተቋማት ትብብር በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማቅረብና የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ÷ የቱሪዝም ዘርፉ በኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ሚና በብቃት እንዲወጣ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብት እጅግ የታደለች ሀገር ብትሆንም አልምቶ መጠቀሙ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ያለውን ሀብት አልምቶ ለመጠቀም ደግሞ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ስምምነቱ የአግልግሎት ጥራትና ደረጃውን ከማሻሻል፣ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር፣ ዘርፉን ከማዘመን እና በተለይ ለሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጪ ሀገር የስራ ገበያ አስተዋጽኦ ከማድረጉ ያለፈ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.