Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ቆጵሮስ የልማት ስራዎችን በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ቆጵሮስ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በግብርና መስኮች በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ከቆጵሮስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ቴሳሊያ ሳሊና ሻምቦስ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ÷የሁለቱን ሀገራት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና በተለይም÷ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በግብርና መስኮች በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የተወያዩ ሲሆን በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል፡፡

አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት እንዲሁም ድህነትን አስወግዶ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በመንግስት በኩል እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት ለዳይሬክተር ጀነራሏ ማብራራታቸው ተገልጿል።

ዳይሬክተር ጀነራሏ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያልተገደበ እርዳታ እንዲደርስ የወሰደው እርምጃ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላት ወደ ህግ እንዲቀርቡ ማድረጉ፣ እንዲሁም ብሄራዊ ምክክር እንዲደረግ የተጀመሩ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው ማለታቸውን በጣሊያን ከኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.