Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ ገቢዎች ቢሮ አማራጭ የግብር ክፍያ ስርዓት ተግባራዊ ማድረጉን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በተያዘው በጀት ዓመት አማራጭ የግብር ክፍያ ስርዓት ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ እንደገለጹት÷ የበጀት አመቱ የግብር መክፈያ ጊዜ ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በይፋ ተጀምሯል፡፡
የግብር ማሳወቂያ ጊዜ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 01 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014፣ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 01 እስከ ጳጉሜ 05 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲሁም የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 01 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም መሆኑን ገልፀዋል።
በ2015 በጀት አመት 70 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው÷ ከሐምሌ 01ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም የዕቅዱን 42 በመቶ ለማሳካት ታቅዷል ነው ያሉት።
በቢሮው የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን እና የተለያዩ አማራጭ የግብር መክፈያ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።
ከኢትዮ- ቴሌኮም ጋር ስምምነት በማድረግ ግብር ከፋዮች በቴሌ ብር በኩል ክፍያ እንዲፈፅሙ እና በኤሌክትሮኒክ ታክስ መክፈል የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ ገልጸው÷ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በተቀመጠላቸው የግብር መክፈያ ጊዜ ተገኝተው በቀረቡላቸው የክፍያ አማራጮች እንዲከፍሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ግብር ሲከፍሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አቶ ፈቃዴ አሰፋ እና አቶ ሰለሞን ይርጉ÷ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መክፈል ለሁሉም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብር ክፍያ ወቅት ከኔትወርክ እና ሲስተም ጋር የሚስተዋሉ ችግሮች በዘላቂነት መፈታት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.