Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ጥሪዎች ዳያስፖራው ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞች ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል እንዳስቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተከታታይ እየተካሄዱ ያሉ ሀገራዊ ጥሪዎች ዳያስፖራው ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞች ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል እንዳስቻሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ ገለጹ፡፡

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል እና የስልጤ ዞን አስተዳደር ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጋር በመተባበር ከኢድ እስከ ኢድ ምዕራፍ ሁለት ጥሪን ተከትሎ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት መድረክ አዘጋጅቷል፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት መርሐ ግብር ሴክሬታሪያት አስተባባሪ ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ ፥ ኢትዮጵያ እየገጠሟት ያሉ ጫናዎችን በማቃለል፣ የሀገራዊ ጥቅሞች አምባሳደር በመሆን፣ በልማትና በበጎአድርጎት ስራዎች ላይ በስፋት በመሳተፍ ዳያስፖራው እያሳየ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት ከዳያስፖራ ተሳትፎ አንጻር በሁሉም ዘርፎች እመርታዊ እድገት የታየበት እንደነበር አንስተው ፥ በተከታታይ እየተካሄዱ ያሉ ሀገራዊ ጥሪዎች ዳያስፖራው ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞች እንዲቆምና ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዳያስፖራውና በሀገር ቤት መካከል ያለው ግንኙነት በየጊዜው በማደግ ላይ ከመሆኑም በላይ ወቅታዊ ሁኔታዎችን የተሻገረና በዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

መድረኩ ዳያስፖራው በክልሉ ካሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ጋር የሚተዋወቅበት፣ ክልሉን በጥልቀት ለመረዳት ዕድል የሚያገኝበትና ለቀጣይ ተሳትፎ መሰረት የሚጥልበት እንደሚሆንም አመላክተዋል፡፡

የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀልጌዮ ጅሎም በበኩላቸው ፥ በክልሉ ኢንቨስትመንት ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል በዋነኝነት እንደሚጠቀስና ከዳያስፖራ የሚቀርቡ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ በልዩ ሁኔታ ዝግጅት እንደተደረገ ገልጸዋል።

የዳያስፖራ የተሳትፎ ፍላጎት ይበልጥ ለማትጋት ክልሉ የመዋቅርና የአደረጃጀት እንዲሁም የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ፥ ዳያስፖራው በወቅታዊ ሁኔታዎች ሳይገደብ የጀመረውን አበረታች ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.