Fana: At a Speed of Life!

በሕክምና የሚታዩ ስህተቶችን ለመቀነስ የሙያ ክህሎትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ የሚታዩ የሕክምና ስህተቶችን ለመቀነስ ለባለሙያዎች የተግባቦትና የሙያ ክህሎት ስልጠናዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የአዲስ አበባ የምግብ፣ መድኃኒት፣ ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ወቅት በሚያጋጥሙ የሕክምና ስህተቶችና የስነ-ምግባር ግድፈቶች ላይ ከጤና ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡

በሕክምና ስህተት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የሚቀበለው የጤና ባለሙያዎች የስነ-ምግባር ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ገላኔ ሌሊሳ ፥ ለኮሚቴው እየቀረቡ ያሉ የሕክምና ስህተት ቅሬታዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ኮሚቴው ከተቋቋመበት 2007 ዓ.ም.ጀምሮ 216 የሕክምና አገልግሎት ስህተትን የተመለከቱ ቅሬታዎችን መቀበላቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 131 በግል ጤና ተቋማት 74 ደግሞ በመንግሥት ጤና ተቋማት ላይ የቀረቡ ሲሆኑ ፥ 116 ቅሬታዎች ውሳኔ ማግኘታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የሕክምና ባለሙያዎች የተግባቦት ክፍተት፣ የታካሚውን የሕመም ታሪክ በደንብ ሰንዶ አለመያዝ፣ አሰራሩ ዘመናዊ አለመሆንን የህክምና ስህተት ቅሬታዎች እየጨመሩ እንዲመጡ አድርጓል ብለዋል፡፡

የተግባቦት፣ የሕይወት ክህሎትና ሌሎች ሥልጠናዎችን በተከታታይነት በመስጠት በሕክምና ስህተት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን መቀነስ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የሕክምና ባለሙያዎችም በሙያተኞች ዘንድ የህክምና አሰጣጥ ችግሮች መኖራቸውን በማመን ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ የምግብ፣ መድኃኒት፣ ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ታደሰ አጥላባቸው በበኩላቸው ፥ በጤና ተቋማት በቸልተኝነትና በክህሎት ማነስ የህክምና ስህተት እንደሚፈጠር አንስተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከክህሎት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በጤና ተቋማት ላይ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለማቅረብ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በመጥቀስ የሙያ ማህበራት፣ የሕክምና ተቋም ኃላፊዎችና ሙያተኞች የድርሻቸውን እንዲወጡም ተጠይቋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.