ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት 8 ዕጩዎች ቀረቡ
አዲስ አበባ፣ሀምሌ 6 ፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት ሥምንት ዕጩዎች መቅረባቸውን ጉዳዩን የያዘው የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገልጿል፡፡
ለእንግሊዙ ወግ አጥባቂ ፓርቲ በመሪነት ለመወዳደር ዕጩ ሆነው የቀረቡት ÷ ሪሺ ሱናክ፣ ሊዝ ትሩስ፣ ኬሚ ባዴኖች፣ ፔኒ ሞርዳውንት፣ ሱኤላ ብራቨርማን፣ ጄረሚ ሀንት፣ ናዲም ዘሃዊ እና ቶም ቱገንድሃት መሆናቸውን ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ሳጂድ ጃቪድ እና ሬህማን ቺሽቲ የተባሉት ዕጩዎች በምርጫው የመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው የነበረ ቢሆንም ፣ የመጨረሻው የዕጩዎች ዝርዝር ከመገለጹ በፊት ራሳቸውን ከውድድሩ ስለማግለላቸው ተገልጿል፡፡
የመጀመሪው ዙር ውድድር በዛሬው ዕለት የሚጀመር ሲሆን ፣ ዕጩዎቹ ወደ መጨረሻው የመሪነት ውድድር ዝርዝር ውስጥ ለመግባት ቢያንስ 20 ድምፆችን ማግኘት እንደሚጠበቅባቸው ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡