Fana: At a Speed of Life!

የቻይና እና የአሜሪካ ውጥረት የብሪክስን መስፋፋት እያጠናከረው መጥቷል – ዘ ዲፕሎማት

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት ብሪክስ በመባል የሚታወቀው የብራዚል፣ ሩስያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና የደቡብ አፍሪካ ቡድንን የማስፋፋት እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲጠናከር ማድረጉ ተጠቆመ።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በሰኔ ወር መገባደጃ ላይ በቤጂንግ በተካሄደው 14ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፥ ቡድኑን የማስፋፋት ሂደት በሚፋጠንበት ሁኔታ ላይ አፅንዖት መስጠታቸውን ተከትሎ ኢራን እና አርጀንቲና ብሪክስን ለመቀላቀል ማመልከቻ አቅርበዋል።

የካዛኪስታን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አርጀንቲና፣ ግብፅ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ታይላንድ እና ሌሎች ተጋባዥ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በግንቦት ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በብሪክስ ስብሰባ ላይ መገኘትም የቡድኑ መስፋፋት እየተፋጠነ እንደሆነ ግልጽ ማሳያዎች መሆናቸውን በኤዥያና ፓሲፊክ አገሮች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩረው ታዋቂ መጽሔት “ዘ ዲፕሎማት” ዘግቧል።

የብሪክስ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያቶችም እያየለ የመጣው የምሥራቅ እና የምዕራቡ ዓለም ግጭት፤ የብሪክስና የደጋፊዎቹ አገራት የትብብር ጥንካሬ እና ከየትኛውም ወገን ያልሆኑና መስቀለኛ መንገድ ላይ የሚገኙ ሀገሮች ፍላጎቶች ሊጠቀሱ እንደሚችሉም ዘገባው አክሏል፡፡

ቻይና ለብሪክሱ አዲስ ልማት ባንክ (ኤንዲቢ) የመጠባበቂያ ገንዘብ ያደረገችው ከፍተኛ የመጠባበቂያ ልገሳም ሌላኛው ተጠቃሽ ምክንያት ነው።

የብሪክስና ሌሎች አገሮች ትብብር ቀስ በቀስ ወደ ኢኮኖሚያዊና የንግድ፣ የፖለቲካ ደህንነትና የህዝብ ለህዝብ እንዱሁም የባህል ልውውጦች እየሰፉ መምጣትም ነው ለአሜሪካ አልዋጥልሽ ያላት ይላል ዘገባው።

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት እና የቻይና አሜሪካ ፉክክር መካከል እየተጠናከረ ያለው አዲስ አውድ ውስጥ በምሥራቁ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ያለውን ግጭት እየጨመረ እንዲሄድ አድርጎታል ተብሏል፡፡

የምሥራቅ እና ምዕራባውያን አገራት ግጭት ይበልጥ በጠነከረ ቁጥር የብሪክስ መስፋፋትን እንደሚያጠነክረውም ነው ዘገባው ያመላከተው።

በፈረንጆቹ እስከ 2017 ድረስ ቻይና የብሪክስ ስብሰባን በተሳካ ሁኔታ ስታስተናግድ እና የብሪክስ አባላትንና የሌሎች አገራትን የትብብር መንገድ በይፋ ባቀረበችበት ወቅት፥ የብሪክስ ትርጉም ከአምስት አባል ሀገራት በላይ ሊደርስ እንደሚችል አመላካች ነበር ነው ያለው ዘ ድፕሎማት።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.