Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ለመተግበር እየተዘጋጀች መሆኗ ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ለመተግበር በዝግጅት ላይ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ÷ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ (የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ) ከመደበኛው የመንግሥት ለመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ጎን ለጎን የሚተገበር መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህ አካሄድ የተለያዩ የሕዝብ አደረጃጀቶችን በማሳተፍ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

የሃይማኖት መሪዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የንግድ ዘርፍ መሪዎች፣ የሚዲያና የትምህርት ተቋማትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ውስጥ እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል፡፡

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አካሄድ ከነባሩ የዲፕሎማሲ መንገድ በተሻለ መልኩ በሕዝቦች መካከል ተዓማኒነት እንዳለው ገልጸው÷ የአገርን ጥቅምና ፍላጎት በቀላሉ ለማስጠበቅና ለማስተዋወቅ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጫና የሚፈጥሩ አካላት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ትልቅ የዲፕሎማሲ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት እስካሁን የነበሩትን ችግሮች በማስተካከል ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ጠንካራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ለመተግበር በዝግጅት ላይ እንደሆነ መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል ፡፡

የሚተገበረው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ ወዳጆችና አጋሮች ባሉበት ሁሉ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመው÷ በሰሜን አሜሪካ፣ በላቲን አገራት፣ በኤሽያ፣ በአፍሪካና ሌሎች ወዳጆች ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሥራው ይጠናከራል ነው ያሉት፡፡

ለሂደቱ ስኬታማነት እንደ ባህልና ስፖርት፣ ቱሪዝም፣ ሰላም ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማትን እንደ ባለድርሻ ለማሳተፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን የተናገሩት አምባሳደር ዲና÷ በአገር ውስጥም ቢሆን በስድስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላት መቋቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.