Fana: At a Speed of Life!

በክረምቱ የበጎ ፈቃድ ወቅት ዜጎች በንቃት ደም እንዲለግሱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወገኖች የደም እጥረት እንዳያጋጥማቸው በተዘጋጁ የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ መርሐ ግብሮች ላይ ዜጎች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ደም ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በርካታ ደም ከትምህርት ተቋማት ይሰበሰባል።
ጊዜው የትምህርት ተቋማት የሚዘጉበት ወቅት በመሆኑ፥ የደም እጥረት እንዳይከሰት ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በአቅራቢያው በሚገኙ የደም ባንክ መሰብሰቢያ ተቋማት ደም እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር እንደ ሀገር በሦስት ወራት ውስጥ እስከ 100 ሺህ ዩኒት ደም ለመለገስ መታቀዱን ገልጸው፥ ለዚህ ዕቅድ መፈጸም በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ወገኖች በንቃት ሰብዓዊ ተግባራትን እንዲፈጽሙ ጠይቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ብቻ እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ድረስ 33 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት አቶ ሀብታሙ፥ ለዚህም በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ አደባባዮች ድንኳኖች መዘጋጀታቸውን እና በጤና ሚኒስቴር ግቢ በሚገኘው የደም ባንክ አገልግሎት እና ስታዲየም በሚገኘው የቀይ መስቀል ግቢ በአጠቃላይ 13 የደም መለገሻ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም 397 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ፥ 337 ሺህ 770 አካባቢ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልጸው ይህም የዕቅዱን 85 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ ሀገር 43 የደም ባንኮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ሃብታሙ፥ በሰሜን የሀገሪቱ ግጭት ምክንያት በትግራይ ክልል ያሉት ሶስት የደም ባንኮች ያሉበት ሁኔታ እንደማያውቁ እና በአማራ ክልል ደግሞ አራት የደም ባንኮች ለተወሰነ ጊዜ ደም መሰብሰብ አለመቻላቸውን ነው የተናገሩት።
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.