Fana: At a Speed of Life!

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ22 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ በአስፋልት ደረጃ እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ22 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር መንገድ በአስፋልት ደረጃ እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘርፍ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በሚሰጡት አገልግሎት ዙሪያ ከሕዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ መድረክ አካሂዷል።

በምክር ቤቱ ቀርበው ገለጻ ፥ ከሰጡ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመንገዶች ግንባታ በፍጥነት አለመጠናቀቅ፣ የጥራት ችግሮችና ተደራሽነት ላይ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በሰጡት ማብራሪያ፥ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የመንገድ ሽፋኑን ወደ 245 ሺህ ኪሎ ሜትር ከፍ ለማድረግ እቅድ መያዙን አስታውሰው ለዚህም የሚረዱ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ22 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር መንገድ በግንባታ ላይ መሆኑን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚጠበቀው ጊዜ ያለመጠናቀቅ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ፥ የወሰን ማስከበር ችግሮች፣ የጸጥታና የተቋራጮች አቅም ማነስ መንስኤዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፕሮጀክት ጊዜና ፋይናንስ አቅርቦት አለመጠናቀቅ፣ በክልል እና ፌደራል መንግስት የሚገነቡ መንገዶችን ያለመለየት ችግሮችንም በምክንያትነት አንስተዋል።

አስተዳደሩ ለካሳ ክፍያ ብቻ 10 ቢሊየን ብር ወጪ ማድረጉን የተናገሩት ኢንጂነር ሀብታሙ ፥ የካሳ ክፍያ አሰራሩም በድጋሚ ሊታይ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አስተዳደሩ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ፖሊሲና አዋጅ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አንስተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ተደራሽነትን ለማስፋት አዳዲስ አሰራሮችን እያስተዋወቅን መሆኑን ያነሱ ሲሆን ፥ ዓለም አሁን የደረሰበትን የአምስተኛው ትውልድ /5ጂ/ አገልግሎትንም በሙከራ ደረጃ መተግበር መጀመሩን አንስተዋል።

ኩባንያው ባለፉት ሦስት ዓመታት የለውጥ ስራዎች ተግባራዊ ማድረጉን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፥ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ በትኩረት መሰራቱን አብራርተዋል።

በቴሌኮም አገልግሎት ላይ መቆራረጥ እየተከሰተ ያለው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት እንደሆነ ገልጸው፥ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ስርቆት፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና የጸጥታ ችግሮች ለአገልግሎቶች መቋረጥ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ከህዝቡ በሚነሱባቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ያላቸውን ምላሽ አዳምጧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.