Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ሰሞኑን የወጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ  ውድቅ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሐምሌ 1 ቀን 2014 ያወጣውን የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዕጣ ውድቅ አደረገ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ÷  ባሳለፍነው ሐምሌ 1 ቀን 2014 የወጣው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውድቅ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጉዳዩን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ “የሕዝብ አመኔታን መቼም ቢሆን አንዘነጋም፤ ክብራችን ሕዝብን በፍትሃዊነት ማገልገል ስለሆነ ሌቦችና እምነታቸውን ሽጠው የሚበሉ ሁሉ ለጊዜው ቢታገሉንም አያሸንፉንም፤ እውነት ምንግዜም ታሸንፋለች” ብለዋል፡፡

የሕዝብን ሀብት በቴክኖሎጂ ውንብድና ከመዘረፍ ማዳን እንደተቻለ የገለጹት ከንቲባዋ ፥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ አወጣጥ ስራ ላይ አጠራጣሪ ጉዳዮች ካጋጠሙ ጊዜ አንስቶ በማጣራት ሂደት ለደገፉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንሲ፣ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዕጣው የተሰረዘውም  የከተማ አስተዳደሩ ከዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓቱ በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች በመቅረባቸው የኦዲት ሥራ ሲጀመር በባንክ የተላከውና ለእጣ እንዲውል ወደ ኮምፒዩተር የተጫነው ዳታ ልዩነት መኖሩ በመረጋገጡ ነው ተብሏል፡፡

በእጣው የሚካተቱት 79 ሺህ ቆጣቢዎች መሆን ሲገባው ÷ ምርመራ ሲደረግ ግን በእጣው ውስጥ የተካተቱት ሰዎች ቁጥር 172 ሺህ መሆኑ ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡

ይህ ማለትም 93 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በተጭበረበረ መንገድ ዕጣ በሚያወጣባት የቴክኖሎጂ ሲስተም ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ሐምሌ 01 ቀን 2014 በወጣው የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ  የዳታ ማጭበርበር ድርጊት በመከሰቱ ሁኔታውን እያጣራ እንደሚገኝ እና በድርጊቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሆነ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በዙፋን ካሳሁን

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.