Fana: At a Speed of Life!

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ የተከሰሱበትን ወንጀል ፖሊስ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዳይሬክተር የማነ ወ/ማሪያም ጋር በመመሳጠር ለእርዳታ የተዘጋጀን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን ለግል ጥቅም አውለዋል በሚል በሙስና እና ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ተጠርጥረው በዛሬው ዕለት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ፖሊስ ባደረገው የማጣራት ስራ ያገኘው የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ የተከሰሱት፥ ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዳይሬክተር የማነ ወ/ማሪያምና ከሌሎችም ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር በተረጂዎች ስም ለኦሶሲዬሽኑ ከተሰጠው የእርዳታ እህልና የምግብ ቁሳቁስ ጋር በተያያዘ የተፈፀመ የሙስና እና ህገ ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሙስና ወንጀል፤
በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል እና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቀድሞ ሲከናወን በቆየው የምርመራ ስራ እንዳረጋገጥነው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዳይሬክተር የማነ ወ/ማሪያም እና ከሌሎችም ሰራተኞች ጋር ያልተገባ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር በሺዎች በሚቆጠሩ በሌሉ ተረጂዎችና ስም እንዲሁም የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ለበርካታ ጊዜያት እህልና የምግብ ቁሳቁሶች ከኮሚሽኑ መጋዘን ካወጡ በኃላ እህሉ ለተረጂዎች ሳይደርስ ለዱቄት ፋብሪካዎችና ለሌሎች ግለሰቦች በሚሊዮን ብሮች በመሸጥ ህገወጥ ጥቅም ሲያገኙ የነበረ መሆኑን፣ ለዚህም ስራቸው አቶ ምትኩ ካሳ በቤተሰቦቻቸው ስም ከሌልሻዳይ ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት በሚሊየን ብር የሚገመት ጥቅም ያገኙ እንደነበረ በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የፌደራል ዋና ኦዲተር የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የግብረሰናይ ድርጅቱ ማዕከላት ላይ በጉዳዩ ላይ ሲያከናውን የቆየው የምርመራ ኦዲት ተጠናቆ የምርመራው አካል ተደርጓል፡፡

1. ምርመራ እየተጣራባቸው የሚገኙ የወንጀል ድርጊቶች
– በሌሉ ተረጂዎች እንዲሁም የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እህልና ቁሳቁሶችን ከኮሚሽኑ በመውሰድ ለተረጂዎች ሳያደርሱ በመሸጥ ለግል ጥቅም ማዋል፣
– ብድርና ድጋፍ በሚል ሰበብ በህገወጥ መንገድ ከኮሚሽኑ በመቶ ሚሊየን ብሮች ለእርዳታ ድርጅቱ በገንዘብ መልክ መስጠት፣
– ኤልሻዳይ ከተባለው ድርጅት ለአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር እና ቤተሰቦቻቸው የተገዙ ቤቶች፣ መኪኖች፣ ገንዘብና ሌሎች የጥቅም ትስስሮች፣

2. አላግባብ በሌሉ ተረጂዎች ስም እንዲሁም የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ወጪ ተደርጎ ለኤልሻዳይ ተራድኦ ድርጅት የተሰጠና ለግል ጥቅም የዋለ አጠቃላይ መጠን፣

 472 ሚሊየን ብር
 ግማሽ ቢሊየን ብር የሚገመት 512 ሺህ ኩንታል ስንዴ
 34 ሺህ ኩንታል በቆሎ
 77 ሺህ ሊትር ዘይት
 4 ሺህ ኩንታል ሩዝ ከተራድኦ ድርጅቱና የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መመሳጠር ለግል ጥቅም ውሏል፡፡

3. የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዋና ዳይሬክተር አቶ የማነ ወ/ማሪያም በርሀ እና ተባባሪዎቹ በተረጂዎች ስም ከወሰዱት እህልና የምግብ ቁሳቁሶች ውስጥ ለተረጂዎች ሳያደርስ ለግል ጥቅም መዋሉን የሚያሳይ፣

 ድርጅቱ ኤልሻዳይ በተረጂዎች ስም ከብሔራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን የወሰደውን የእርዳታ ስንዴ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ለሚገኝ ሶሮሮ ጠ/ን/ሥ/ኃ/የተ/የግ/ማህበር እህት ኩባንያ ለሆነው ኪያ ዱቄት ፋብሪካ 66,483 ኩንታል ስንዴ በብር 66,483,880.00 በመሸጥ ገንዘቡን የወሰዱ በመሆኑ፣
 በተመሳሳይ ኤልሻዳይ ሶሮሮ ትሬዲግ የተባለ ድርጅት ከሚያስመጣቸው መኪኖች ውስጥ 4 (አራት) ደብል ገቢና ፒካፕ መኪኖችን በብር 6,450,000.00 ለእርዳታ በሚል በወሰደው 6,450 ኩንታል ስንዴ በመለወጥ መኪኖቹን የወሰደ በመሆኑ፣
 ኤልሻዳይ ለነጃ ሄሬዲን ወይም ሂራ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ 15,000 ኩንታል ስንዴ በብር 15,000,000.00 በመሸጥ ገንዘቡን የወሰደ በመሆኑ፣

4. እስካሁን በተደረገው ምርመራ ብቻ አቶ ምትኩ ካሳ እና ቤተሰቦቻቸው ከኤልሻዳይ ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንደ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን በተሰጠ ገንዘብ በቤተሰቦቻቸው ያፈሩት ንብረት፣

4.1. በልጁ ስም ከኤልሻዳይ ድርጅት በተላለፈ ገንዘብ ቶዮታ ኮሮላ መኪና ተገዝቶለታል፡፡ በተጨማሪም ልጁ ከ13/2/2009 ዓ.ም ጀምሮ ኤልሻዳይ ድርጅት በወር ብር 15 ሺህ እየከፈለለት ሙሉ ግቢ ቤት ተከራይቶለት ይኖር ነበር፤

4.2. በሁለተኛ ልጁ ስም የኤልሻዳይ ድርጅት ተቀጣሪ ሳትሆን በድርጅቱ ፔይሮል ውስጥ ስሟ ተካቶ ለ1 ዓመት ያክል በወር 5 ሺህ ብር ደመወዝ ሲከፈላት የቆየ ከመሆኑም በተጨማሪ ከኤልሻዳይ ድርጅት ብር 893 ሺህ 25 ገቢ የተደረገላት መሆኑ፤

4.3. በባለቤቱ ስም (በወኪል የኤልሻዳይ ድርጅት ዋና ስራአስኪያጅ) ከኤልሻዳይ ድርጅት ሂሳብ ወጭ በተደረገ ብር 8 ሚለየን 306 ሺህ 737.75 የቦታ ስፋት 388.75 ካሬ ሜትር የሆነ በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ አፓርታማ የተገዛላት መሆኑ፣

4.4. በተጨማሪም በባለቤቱ ስም በደቡብ ክልል ሃዋሳ ከተማ በ9.8 ሚሊዮን ብር 400 ካሬ ሜትር G+3 የሆነ ቤት ከኤልሻዳይ ድርጅት ወጪ በሆነ ገንዘብ የተገዛላት መሆኑ፡፡ ቤቱ በኤልሻዳይ ድርጅት ለባለቤቱ ከተገዛላት በኃላ መልሶ እልሻዳይ ድርጅት እንዲከራየው ተደርጓል፡፡

4.5. ባለቤቱ ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል ሰላሙ ስም በተጨማሪ በቦሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ 12 እንይ ሪል ስቴት አንድ ቤት የተገዛላት መሆኑ
4.6. ለወላጅ እናቱ ወ/ሮ ኢቲኮ አጌቦ ጆሀር ከኤልሻዳይ የግብረሰናይ ድርጅት ድርጅት በሲፒ.ኦ ገቢ የተደረገ ብር 5,000,000.00 (አምስት ሚሊየን)፣

4.7. ከኤልሻዳይ የግብረሰናይ ድርጅት በተሰጠ ብር በእናቱ ወ/ሮ ኢቲኮ አጀቦ ጁሀር ስም የተገዙ 7 /ሰባት/ ቤቶች፣

4.8. በወላጅ እናቱ ወ/ሮ ኢቲኮ አጀቦ ጁሀር በስማቸው በተከፈቱ ሁለት የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች ወደ 19.5 ሚሊየን ብር በላይ እንቅስቃሴ ያሳያሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.