Fana: At a Speed of Life!

ሰው በማገት 212 ሺህ 450 ብር የተቀበለው ግለሰሰብ በ17 አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰው በማገት 212 ሺህ 450 ብር የተቀበለው ግለሰሰብ በ17 አመት ፅኑ እስራት መቀጣቱን የመተማ ወረዳ ፍትህ ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ተከሳሹ አቶ ታደለ ፀጋ ፈንቴ በጭልጋ ወረዳ ሰራቫ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ጥቅምት 27 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:00 ላይ ከገንዳ ውሃ ከተማ ወደ መቃ ቀበሌ አራት ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረን ባጃጅ በጦር መሳሪያ በማስፈራራት ባጃጁ ውስጥ የነበሩትን አራት ሰዎችን አግቷል።

ሰዎችን ካገተ በኋላም ወደ ሌንጫ ቀበሌ ጫካ ውስጥ በመውሰድ ገንዘብ ካላመጣችሁ እንገድላችሗለን በማለት እስክ ህዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም በማገት ማቆየቱን የወረዳው ዐቃቤ ህግ ካቀረበበት የክስ መዝገብ መገንዘብ ተችሏል፡፡

ከ16 ቀናት እገታ በኋላም ከግል ተበዳዮች በድምሩ 212 ሺህ 450 ብር በመቀበል ህዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ  5:00 ሲሆን ያገታቸውን አራት ግለሰቦች መልቀቁ በፍርድ ሂደቱ ተረጋግጧል፡፡

የወረዳው ዐቃቤ ህግም ከመተማ ወረዳ ፖሊሰ ፅህፈት ቤት ተጣርቶ የመጣለትን የወንጀል ምርመራ መዝገብ በመመርመር ተከሳሹ ተደራራቢ የሰው ማገት ወንጀል የፈፀመ ለመሆኑ በማስረጃ አረጋግጧል፡፡

ክርክሩን ሲመለከት የነበረው የመተማ ወረዳ ፍርድ ቤትም ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ በማስረጃ ያረጋገጠ ሲሆን የጥፋተኝነት ውሳኔ ወስኖበታል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግንና የተከሳሹን የቅጣት አስተያየት በመቀበል ሐምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹን እና መሰል ወንጀል የሚፈፅሙ ግለሰቦችን ያርማል ያስተምራል ያለውን የ17 ዓመት ፅኑ እስራት የቅጣት ፍርድ የወሰነበት መሆኑን ከመተማ ወረዳ ፍትህ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.