Fana: At a Speed of Life!

በ2014 በጀት ዓመት ከአገር ውስጥ የኃይል ሽያጭ እና የፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ ከ15 ነጥብ 79 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የማርኬቲንግና ቢዝነስ ልማት መምሪያተወካይ ዳይሬክተር አቶ ህይወት እሸቱ እንደገለፁት÷ከሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ፣ ከኃይል ኤክስፖርት እና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ 15 ነጥብ 79 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ20 ነጥብ 75 ቢሊየን ብር በላይ ሽያጭ በማከናወ የእቅዱን 107 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡

የተቋሙ የፋይናንስ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ በበኩላቸው÷ ከሽያጩ ውስጥ ከ14 ነጥብ 44 ቢሊየን ብር በላይ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከቀረበ የኃይል ሽያጭ፣ ከ834 ነጥብ 16 ሚሊየን ብር በላይ ከከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች፣ ከ418 ነጥብ 57 ሚሊየን ብር በላይ ለኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር ከቀረበ የኃይል ሽያጭ የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 94 ሚሊየን ብሩ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያና ዌብስፕሪክስ አይሲቲ ሶሉሽን የተባሉ ኩባንያዎች ከተጠቀመበት የፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ የተገኘ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በበጀት ዓመቱ ለሀገር ውስጥ አገልግሎት የሚውል 13 ሺህ 262 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ታቅዶ 10 ሺህ 325 ጊጋ ዋት ሰዓት በማቅረብ የእቅዱን 77 ነጥብ 8 በመቶ ማሳካት መቻሉም ተጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ የተሰበሰበውን ገቢ ለማግኘት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 9 ሺህ 472 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት ሰዓት፣ ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች 7 መቶ 44 ነጥብ 5 ጊጋ ዋት ሰዓት እንዲሁም ለኢትዮ- ጂቡቲ ምድር ባቡር 108 ነጥብ 9 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ መቻሉንም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ተቋሙ በ2014 በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ኃይል ሽያጭና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ የሰበሰበው ገቢ ከ2013 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ1 ነጥብ 98 ቢሊየን ብር በላይ ወይም የ11 ነጥብ 16 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.