Fana: At a Speed of Life!

18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ይጀምራል

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ኦሬጎን የሚካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ይጀመራል።

በውድድሩ ÷ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች በአጠቃላይ 40 ማለትም 21 ወንድና 19 ሴት አትሌቶችን እንደምታሳትፍ ተገልጿል።

አትሌቶቹ በ800 ሜትር፣ በ1 ሺህ 500 ሜትር፣ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል፣ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር እንዲሁም ማራቶን ርቀቶች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

ነገ በውድድሩ መክፈቻ ቀን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማጣሪያ ውድድራቸውን እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል፡፡

ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከሩብ ላይ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች ÷አትሌት ለሜቻ ግርማ፣አትሌት ኃይለማርያም አማረና አትሌት ጌትነት ዋለ የሚወዳደሩ ሲሆን÷ አትሌት አብርሃም ስሜ ደግሞ በተጠባባቂነት እንደተያዘ ተገልጿል፡፡

ነገ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በ1 ሺህ 500 ሴቶች ማጣሪያ ÷አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ፣አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉና አትሌት ሂሩት መሸሻ ይሳተፋሉ የተባለ ሲሆን አትሌት አክሱማዊት አምባዬ በውድድሩ ላይ በተጣባባቂነት ተይዛለች።

በሻምፒዮናው ከ192 አገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 972 አትሌቶች በ50 የአትሌቲክስ ውድድሮች ማለትም ÷49 የግል እና አንድ የቡድን ውድድር እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።

ውድድሩ በኢዩጅን በሚገኘው የኦሬጎን ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ በሚገኘው ሄይዋርድ ፊልድ የአትሌቲክስ ሜዳ የሚካሄድ ሲሆን ÷12 ሺህ 900 ተመልካቾችን ያስተናግዳል ነው የተባለው።

ሻምፒዮናው በአውሮፓና አፍሪካ የሚገኙ ከ40 በላይ የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሜሪካ ሲካሄድ የኦሬጎኑ የመጀመሪያው ሲሆንሻምፒዮናው እስከ ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚቆይ ኢዜአ ዘግቧል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.