Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ2014 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ የገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱሰላም መሀመድ ÷ በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ ዘርፎች 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 2 ቢሊየን 164 ሚሊየን 340 ሺህ 840 ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ገቢው የተሰበሰብውም ከቀጥታ ግብር፣ ቀጥታ ካልሆኑ እና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በዚህ መሰረትም ከቀጥታ ግብር 1 ቢሊየን 21 ሚሊየን 597 ሺህ 960፣ ቀጥታ ካልሆነ ግብር 773 ሚሊየን 105 ሺህ 382 ታክስ ከሆኑ ገቢዎች ደግሞ 50 ሚሊየን 527 ሺህ 407 ብር መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡

ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች ሊሰበሰብ ከታቀደው 434 ሚሊየን ብር ውስጥ 319 ሚሊየን 202 ሺህ 578 ብር የተሰበሰበ ሲሆን ÷ይህም የእቅዱን አፈጻፀም 73 በመቶ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የ2014 በጀት ዓመት የገቢ አፈጻፀም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ142 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡

በተያዘው የ2015 በጀት ዓመትም የገቢ ግብር መሰረቶችን በማስፋት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ ስለመያዙ ተጠቁሟል፡፡

በተሾመ ኃይሉ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.