Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዛሬው ዕለት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያይተዋል።

ኮሚሽኑ ላለፉት 4 ወራት ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ለፕሬዚዳንቷ አብራርቷል።

ለምክክሩ በቅድመ ዝግጅት ላይ የሚገኘው ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ውይይቶችን ማድረጉን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን ዓርአያ ተናግረዋል፡፡

ከክልሎች እና ቁልፍ ከሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር የመምከር እንዲሁም ለምክክሩ መሠረታዊ የሆኑ ንድፈ ሃሳቦችን የማዘጋጀት ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ የተጣለበትን አደራ እና ኃላፊነት በገለልተኝነት እንዲወጣ ድጋፍ እንዲደረግለትም ፕሮፌሰር መስፍን ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ለሌሎች ሀገራት ጭምር በምሳሌነት የሚጠቀስ እንዲሆን ኮሚሽኑ ያለምንም ጫና ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ለዚህም ለኮሚሽኑ አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር እንደሚደረግም ፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ አረጋግጠዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ሀገራዊ ምክክሩ ላለፉት 2 ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያጋጠሙ አለመረጋጋቶች፣ የዜጎች መፈናቀል እና ጉዳትን ለመከላከል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ጠቅሰው ኮሚሽኑ ሚናውን በኃላፊነት እንዲወጣ ማሳሰባቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.