Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ 161 ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ቦታዎች ተለይተዋል- የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በ61 ቦታዎች ላይ 161 የሚሆኑ በተለያየ መጠን የሚገኙ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር በመለየት ለሚመለከታቸው አካላት ማድረሱን የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ከክረምቱ ማየል ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ ጎርፍን ጨምሮ ከድንገተኛ አደጋዎች እራሱን ሊጠብቅ ይገባል፡፡
በያዝነው ክረምት በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መከላከልን በማስቀደም በልዩ ትኩረት ሰባት ሴክተር መስሪያ ቤቶች በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባካሄደው የተጋላጭ ጥናት በ61 ቦታዎች ላይ 161 የሚሆኑ በተለያየ መጠን የሚገኙ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች መለየታቸውን ገልጸው÷ የጥናት ውጤቱን ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር በማጣመር ለሚመለከታቸው አካላት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ በአስተዳደሩ በኩል የሚሠራው ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ÷ ህብረተሰቡ ለጎርፍ አደጋ የሚያጋልጠውን አሠራር ተረድቶ እራሱን ሊከላከል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በክረምት ጊዜ የአየር ንብረት ሁኔታውን መሰረት አድርጎ÷ በዋናነት የጎርፍ እንዲሁም የኤሌክትሪክ፣ ከሕንጻ ግንባታዎች ጋር የተያያዙ፣ ቅዝቃዜን ለመከላከል ሲባል በቂ የአየር ዝውውር በሌለበት ሁኔታ ከሰል መጠቀም፣ ከግንባታ ሥራ ጋር በተያያዘ የተቆፋፈሩ አካባቢዎች እና የትራፊክ አደጋዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡
ከግንቦት ወር ወዲህ በቀጥታ ከጎርፍ ጋር በተያያዘ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን እና ከውሃ እንቅስቃሴና ከዋና ጋር በተያያዘም የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮው ክረምት ከመግባቱ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው÷ ህብረተሰቡ ለሥራም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ሲንቀሳቀስ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዝናቡን ተከትሎ ልጆች ለዋና እና ጨዋታ በሚል ወደ ወንዝ እንዳይሄዱ ወላጆች ክትትል እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
አደጋዎች ሲያጋጥሙም ህብረተሰቡ በ939 ነጻ የስልክ መስመር ወይም በ011 1 55 53 00 ላይ በመደወል ሪፖርት እንዲያደርግም ነው የጠየቁት።
በ2013 ዓ.ም የክረምት ወቅት ባጋጠሙ 25 የጎርፍ አደጋዎች የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና 4 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ንብረት መውደሙን አቶ ንጋቱ አስታውሰዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.