Fana: At a Speed of Life!

41ኛው የአፍሪካ ኅብረት የአስፈጻሚዎች መደበኛ ስብሰባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 41ኛው የአፍሪካ ኅብረት የአስፈጻሚዎች መደበኛ ስብሰባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ አስተናጋጅነት የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት የአስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በይፋ ተጀምሯል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክም በስብሰባው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
መደበኛ ስብሰባው ሲጀመር የኅብረቱ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ባደረጉት ንግግር ÷ በአፍሪካ ምጣኔ ሐብታዊ ትሥሥር በማምጣቱ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ገልፀዋል።
ሊቀ መንበሩ ÷ ከአኅጉሪቱ ድኅነትን ለማስወገድ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ለሚሰሩ ሥራዎች ዓለምአቀፍ አጋሮች እና የግሉ ዘርፍ ቁልፍ ሚና መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያዎችን በመተግበር ላይ እንደሆነ በንግግራቸው ያስታወሱቱ ሙሳ ፋኪ ÷ ማሻሻያዎቹ ኮሚሽኑን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉት ናቸው ብለዋል።
የስብሰባው አዘጋጅ የሆነችው ዛምቢያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ስታንሌ ካኩቦ በኩል ÷ የአፍሪካ ኅብረት በዚህ ዓመት በአጀንዳነት የያዘውን የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ በአኅጉሪቱ የማረጋገጥ ዕቅድ ዕውን ለማድረግ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመኑ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አፍሪካ በኢንቨስትመንት እና ንግድ ላይ ዘላቂ ዕድገት ለማስመዝገብ የሠላም ግንባታ ላይ መዕዋለ ንዋይዋ መድባ መሥራት አለባት ብለዋል።
የኅብረቱ የአስፈፃሚዎች ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የሴኔጋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሳታ ቶል ሳል የመክፈቻ ንግግር ማድረጋቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ስብሰባው የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል ራሱን ችሎ በሚሠራበት አግባብ ላይ ተጨማሪ ሥልጣን ስለ መስጠት ይመክራልም ተብሏል።
በመደበኛ ስብሰባው የቀጣዩ ዓመት የኅብረቱ በጀት የሚጸድቅ ሲሆን በቅርቡ የተመሰረተው የአፍሪካ መድሃኒት ኤጀንሲ ዋና መቀመጫ አስተናጋጅ ሀገር የሚመረጥም ይሆናል ተብሏል።
በተጨማሪም የኅብረቱ ተቋማዊ የማሻሻያ ሥራዎች የደረሱበት ደረጃ ተገምግሞ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከ41ኛው የአስጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በተጨማሪ በሉሳካ የኅብረቱ ቢሮ አባላት እና የክፍለ አኅጉራዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች ሊቃነ-መናብርት የሚሳተፉበት ቅንጅታዊ ጉባዔም ይካሄዳል።
በስብሰባው ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.