Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ከተማ የሠዓት ዕላፊ ተጣለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በጋምቤላ ከተማ የሚታዩ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የሠዓት ዕላፊ ገደብ መጣሉን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽኅፈት ቤት አስታወቀ።

በመሆኑም በጋምቤላ ከተማ የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ከምሽቱ 2 ሠዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 11 ሠዓት 30 ድረስ መገደቡን እና ተግባራዊ እንዲደረግ ውሳኔ መተላለፉን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽኅፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ ገልጸዋል።

የሠዓት ዕላፊው የድንገተኛ ሕክምና ማመላለሻ አምቡላንስ እና የጸጥታ ኃይል ተሽከርካሪዎችን እንደማይመለከት ተጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ከተማ ሠላማዊ ሁኔታ መኖሩን ያመለከቱት ኃላፊው ፣ በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች የተጠናከረ ጥበቃ እያደረጉ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

አቶ ኡገቱ ÷ የጸጥታ ኃይሉ የከተማውን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ኅብረተሰቡ በየአካባቢው ተደራጅቶ መረጃ በመስጠት ጭምር እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ቀደም በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ መደፍረስ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሠዓት ዕላፊ ተጥሎ እንደነበር ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.