Fana: At a Speed of Life!

ለሕጻናት ሁለንተናዊ ዕድገት በጨዋታ ማስተማር – ከጓቲማላ ተሞክሮ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕጻናት ሁለንተናዊ ዕድገት የተሻለ ለማድረግ ወላጆች ጊዜ ሰጥተው በጨዋታ ማስተማር እንደሚችሉ ተገለፀ፡፡

ቻይልድ ፈንድ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ከጓቲማላ በተገኘ ተጨባጭ ተሞክሮ ወላጆች ለሕፃናት ትኩረት በመስጠት እና በጨዋታ በማስተማር ሁለንተናዊ ዕድገታቸው ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡

በሀገራችን በአማራ፣ በኦሮሚያ እንዲሁም በደቡብ ክልሎች እና በአዲስ አበባ ተግባራዊ የሚያደርገውን የሬዲዮ መልዕክትን መሠረት ያደረገ ፕሮጀክትም ቻይልድ ፈንድ ይፋ አድርጓል፡፡፡

ሁነቱን በክብር እንግድነት ተገኝተው በንግግር የከፈቱት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሙድ፥ ለሕፃናት ሁለንተናዊ ዕድገት የወላጆችና የአሳዳጊዎች ሚና የማይተካ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ተገቢውን የማስተማሪያ መንገድ ማወቅም የወላጆችና የአሳዳጊዎች ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሌጎ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የአንድ ዓመት ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረገው ቻይልድ ፈንድ ÷ በኢትዮጵያ በሚገኙ 13 አጋር ድርጅቶቹ አማካኝነትና በሬዲዮ በሚያስተላልፋቸው ጨዋታ አዘል አጫጭር መልዕክቶች ለአንድ ዓመት የሚቆየውን ወላጆችንና አሳዳጊዎችን የማስተማር ሥራ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በጌዲዮኛ እና በክስታኔ ቋንቋዎች ተግባራዊ ያደርጋል ተብሏል፡፡

በይትባረክ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.