Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ ሕግ ተላልፈው በተገኙ ከ367 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል አለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2014 በጀት ዓመት በተደረገ የዋጋ ማረጋጋትና የሕገ ወጥነት ቁጥጥር ሥራ ሕግ ተላልፈው ተገኝተዋል በተባሉ 367 ሺህ 880 ነጋዴዎችና የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማቱ አመራሮች በተቋማቱ የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃጸምና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ በአዳማ ከተማ እየተወያዩ ነው፡፡

የንግድ ሥርዓትና የንግድ ፈቃድ ዘርፍ አማካሪ አቶ ግዛው ተክሌ የዘርፉን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃጸም ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ለተጠሪ ተቋማት አመራሮች አቅርበዋል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባለው የንግድና ቀጣናዊ ትሰስር ሚኒስቴር መዋቅር ዋጋ የማረጋጋት፣ ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ግብረ ሃይል በተሰሩ ስራዎች ህግ ተላልፈው በተገኙ 192 ሺህ 850 ነጋዴዎች ላይ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ 167 ሺህ 592 የንግድ ተቋማትን የማሸግ፣ 3 ሺህ 741 ነጋዴዎችን ከንግድ ስራ የማገድ እርምጃዎች መወሰዱ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በ1 ሺህ 723 ነጋዴዎች ክስ መመስረቱን መገለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

እርምጃ የተወሰደባቸው ያለንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ፣ ያለደረሰኝ የተገበያዩ፣ በምርቶች ላይ ባዕድ ነገር ቀላቅለው ለገበያ ያቀረቡ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች ለገበያ ያቀረቡ እንዲሁም ያለአግባብ ዋጋ የጨመሩ ናቸው ተብሏል፡፡

እርምጃው የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር ያልለጠፉ እና ምርትን ያለአግባብ በክምችት የያዙ ነጋዴዎችንም እንደሚያካትት የንግድ ሥርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ አማካሪ አቶ ግዛው ተክሌ የዘርፉን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃጸም ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች ባቀረቡበት ወቅት አብራርተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.