Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ በ2015 የትምህርት ዘመን ከመመሪያው ውጭ የክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደማይቻል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶች ከመመሪያው ውጪ ወርሃዊ የክፍያ ጭማሪ ማድረግና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎችን መጠየቅ እንደማይቻሉ የአዲስ አበባ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን አሳሰበ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ ፍቅርተ አበራ ÷ መመሪያው በ2014 ዓ.ም ጭማሪ ያደረጉ የግል ትምህርት ቤቶች በ2015 የትምህርት ዘመን ምንም አይነት ጭማሪ እንዳያደርጉ ያዛል ብለዋል፡፡

መመሪያውን በመጣስ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች አስቀድመው በደብዳቤና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ጭማሪ እንደሚያደርጉ ለወላጆች መልዕክት እያስተላለፉ መሆኑ ተደርሶበታል ነው ያሉት።

መመሪያውን በሚጥሱ ትምህርት ቤቶች ላይ ፈቃድ የመሰረዝና በሕግ የማስጠየቅ እርምጃዎች እንደሚወሰድ ከወዲሁ አሳስበዋል።

በከተማው 1ሺህ 590 የግል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን÷ በ2014 የትምህርት ዘመን 1ሺህ 77 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ወርሃዊ የክፍያ ጭማሪ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

ቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች በሚያቀርቡት ፕሮፖዛል እና ከወላጅ ጋር በሚያደርጉት መግባባት ጭማሪ ማድረግ እንደሚችሉም መመሪያው ያዛል ብለዋል።

ማንኛውም ትምህርት ቤት ከመደበኛ የአገልግሎት ክፍያ ውጭ በአይነትም ሆነ በገንዘብ ክፍያ መጠየቅ እንደማይችልም ምክትል ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶችን ሳይጨምር በወር እስከ 15 ሺህ ብር ክፍያ የሚጠይቁ ትምህርት ቤቶች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ይህ የተጋነነ የትምህርት ቤት ክፍያ የሕብረተሰቡን የመክፈል አቅም እየተፈታተነ በመሆኑ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡

ባለፈው ዓመት ወላጆች ባልተስማሙበትና ከባለሥልጣኑ እውቅና ውጭ የተጋነነ ጭማሪ ያደረጉ ትምህርት ቤቶች ላይ ጭማሪውን ለወላጆች ከመመለስ ባሻገር እርምጃ የተወሰደባቸውም እንዳሉ አብራርተዋል።

ወላጆች እነዚህን ትምህርት ቤቶች በማጋለጥና የመማር ማስተማር ሥርዓቱ በአግባቡ እንዲመራ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ምንም ዓይነት ጭማሪ ባለማድረጋቸው ምክትል ሥራ አስኪያጇ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.