Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር በሰላም ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ፊንላንድ አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር በሰላም ለመፍታት የጀመረውን እንቅስቃሴ ፊንላንድ እንደምትደግፍ አስታወቀች።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ ከፊንላንድ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ልዩ ተወካይ ሱልዳን ሰዒድ እና በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ኦቲ ሆሎፖይነን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ፥ የሁለቱን ሀገራት የፓርላማ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
ዶክተር ዲማ ለፊንላንድ ፓርላማ ልዩ ተወካይና ለአምባሳደሯ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን ብትችልም፥ በሂደቱ የተለያዩ ፈተናዎች እንደነበሩም አብራርተውላቸዋል።
በተለይም ፥ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት የሰላም አማራጭን ተከትሎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት ፊንላንድ ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እንድትደግፍም ጠይቀዋል።
ሱልዳን ሰዒድ አህመድ በበኩላቸው፥ ፊንላንድ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት የጀመረውን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ ነው ያረጋገጡት።
በዚህ ረገድም በኢትዮጵያ ሰላምን ማምጣት ዓላማ ያደረገውን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ፊንላንድ ትደግፋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጠናው መሪነቷን ለማስጠበቅ የራሷን ሰላም መጠበቅ እንደሚኖርባት አመልክተው ፥ የሰብዓዊ ድጋፍ በየብስና በአየር ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ በድጋሚ መጀመሩ ፊንላንድ እንደምታደንቅ ም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና ፊንላንድን የፓርላማ- ለፓርላማ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩም ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
ፊንላንድ በቀጠናው ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በሚል የሀገሪቱ ፓርላማ ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም የ29 ዓመቱ ትውልደ-ሶማሊያዊውን ሱልዳን ሰዒድ አህመድን ልዩ ተወካይ አድርጎ መሾሙ የሚታወስ ነው።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.