Fana: At a Speed of Life!

ብሪታንያ በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ልትመታ እንደምትችል የአየር ንብረት ትንበያ መረጃ አመላከተ

በአዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥለው ሳምንት ዋና ከተማዋን ለንደንን ጠምሮ የብሪታንያ አንዳንድ አካባቢዎች በከፍተኛ የሙቀት ሞገድ ሊመቱ እንደሚችሉ የሀገሪቱ የአየር ንብረት ትንበያ ቢሮ አስጠንቅቋል፡፡

ማስጠንቀቂያውን ተከትሎ የአገሪቱ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ታውቋል፡፡

እንደ ሀገሪቱ የአየር ንብረት ትንበያ ቢሮ ከሆነ፥ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች 40 ዲግሪ ሴሊሸየስ የሚደርስ ሙቀት ሊከሰት እና ይህም እስከሞት የሚያደርስ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡

ቢሮው ጉዳዩን አስመልክቶ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን፥ የሙቀት ሞገዱ ለንደንን፣ ማንችስተርን እና ዮርክን ሊያጠቃልል እንደሚችል አስታውቋል፡፡

የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ኤጀንሲ በበኩሉ ከፍተኛ የሙቀት ሞገዱን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ሊከሰት ይችላል ተብሎ የተተነበየው ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል 4ኛ ደረጃ የሚባል ሲሆን፥ ይህም ጉዳት የሚያስከትለው ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ብቻ ሳይሆን ጤናማ ሰዎችንም ጭምር እስከሞት የሚደርስ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ንው የጤና ኤጀንሲው ያስጠነቀቀው፡፡

ከፍተኛ የሙቀት ሞገድ ይከሰትባቸዋል በተባሉ ቦታዎች የሚገኙ ነዋሪዎችም የፀሐይ ሙቀት በሚጨምርበት ጊዜ ወደ ውጭ ከመውጣት እንዲታቀቡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የብሪታንያ መንግሥት ሊከሰት የሚችለውን ሞቃታማ ማዕበል እንደ ብሄራዊ ድንገተኛ አደጋ እንደሚስተናግደው መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.